Wednesday, December 27, 2017

በአሜሪካ የሚገኙ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ስደተኞችን በማስጠለል ላይ መሆናቸው ታወቀ

 በአሜሪካ የሚገኙ በርካታ አብያተ ክርስቲያናት ስደተኞችን በማስጠለል ላይ መሆናቸው ታወቀ። አብያተክርስቲያናቱ ስደተኞቹን እያስጠለሉ ያሉት የትራምፕ አስተዳደር ሕገወጥ የሚላቸውን ስደተኞች ወደ ሀገራቸው የመመለሱን ስራ በማጠናከሩ ነው። ቢያንስ 32 የሚሆኑ አብያተክርስቲያናት በራቸውን ለስደተኞች ክፍት በማድረግ ስደተኞቹን ከመባረር በመታደግ ላይ ናቸው። የአሜሪካ የስደተኞችና ጉምሩክ ሕግ አስከባሪ መስሪያ ቤት ፖሊሲ በአብያተክርስቲያናት ፣በትምህርት ቤቶች እንዲሁም በሕክምና ተቋማት ፍተሻ ማካሄድን አይፈቅድም። በመሆኑም የመኖሪያ ፍቃድ የሌላቸውና ከሀገር እንዲወጡ የተወሰነባቸው ስደተኞች ከመባረር ለመዳን በራቸውን በከፈቱ አብያተ ክርስቲያናት ገብተው ይደበቃሉ። ፖሊሲው ይህን ይበል እንጂ የስደተኞችና ጉምሩክ ህግ አስከባሪዎች በአብያተክርስቲያናትና መሰል ተቋማት እንዳይገቡ የሚከለክል ህግ የለም። አሊሪዮ ጎሜዝ የተባለና ከኤልሳልቫዶር የመጣ ስደተኛ ፍርድ ቤት ወደ ሃገሩ እንዲመለስ በመወሰኑ ከመባረር ለመዳን በአንድ ቤተክርስቲያን ተጠልሎ ይገኛል።
አሊሪዮ ለአልጀዚራ እንደተናገረው ሀገሩ የሚመለስ ከሆነ ሞት ነው የሚጠብቀው። እሱ እንደሚለው ብጥብጥ በነገሰባት ኤልሳልቫዶር በነበረበት ጊዜየግድያ ዛቻ ደርሶበታል። በዚህም ምክንያት ለሱ ወደ ሀገሩ መመለስ ማለት የመሞትና የመኖር ጉዳይ ነው። አሊሪዮ ጎሜዝ እንዳለው በቡድን የተደራጁ ሕገወጥ እጽ አዘዋዋሪዎች በኤልሳልቫዶር ያሻቸውን እንደሚያደርጉ ተናግሯል። እጽ አዘዋዋሪዎቹ ሰላማዊ ሰዎች ሕገወጥ ስራቸውን እንዲያከናውኑላቸው እንደሚያስገድዱና አልታዘዝ ያለውን እንደሚገድሉ ገልጿል። በቫንደርቢልት ዩኒቨርስቲ በተደረገ ጥናት በኤልሳልቫዶር 100 ሺ ከሚሆኑ ነዋሪዎች ውስጥ 82 የሚሆኑት ግድያ ይፈጸምባቸዋል። አሊሪዮ አራት ግዜ ያህል በሕገወጥ ስደተኞች ማሰሪያ ቦታ ገብቶ እንደነበር ይናገራል። ይህ የሕገወጥ ስደተኞች ማጎሪያ ውስጥ በስደተኞች ላይ ብዙ በደል የሚፈጸምበት ቦታ መሆኑን የአሜሪካ የሀገር ውስጥ ደህንነት መስሪያ ቤት ባለስልጣናት ጭምር ያምናሉ። ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት ቃል በገቡት መሰረት ሕገ ወጥ ስደተኞችን የማስወገዱን ስራ አስተዳደራቸው አጠናክሮ ቀጥሏል። ባለፈው ታህሳስ ታራምፕ ፕሬዝዳንት ከሆኑ በኋላ እስከ ባለፈው መስከረም ድረስ ሕገወጥ ስደተኞችን የመያዙ ስራ በ40 በመቶ ጨምሯል።

No comments:

Post a Comment