Friday, December 22, 2017

የኦህዴድ ተወካዮች የፓርላማ ውይይቱ እንዲቋረጥ አደረጉ

ዛሬ ታህሳስ 13/2010 ዓም ኦሮሚያ በአዲስ አበባ ላይ የሚኖራትን ልዩ ጥቅም ለመወያየት የኦህዴድ የፓርላማ አባላት ለውይይት ተጠርተው የነበረ ቢሆንም፣ የኦሮምያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ እና እርሳቸውን ደግፈው የቆሙ የፓርላማ አባላት ባስነሱት ተቃውሞ ውይይቱ እንዲቋረጥ ተደርጎ ፓርላማው ተበትኗል። በቅርቡ ከአፈ ጉባኤ ወንበራቸው ለመነሳት የስልጣን መልቀቂያ አቅርበው የነበሩት አፈ ጉባኤው አባ ዱላ ገመዳ ከአቶ አዲሱ እና ከሌሎች የፓርላማ አባላት የተለዬ አቋምይዘው ታይተዋል።

የኮሚኒኬሽን ቢሮ ሃላፊው አቶ አዲሱ አረጋ ፣ “ 600 ሺ የተፈናቀሉ የኦሮሞ ተወላጆችን በየመጠለያው አስቀምጠንና በመከራ እያኖርን ፣ የጉዳዩ ባለቤት የሆነውን ሕዝቡን እስከታች ወርደን ሳናወያየው እና የጋራ መግባባት ላይ ሳንደርስ ለብዙ ዓመት የቆየን አዋጅ ለማጽደቅ በዚህ ወቅት በዚህ አጀንዳ ላይ ለመነጋገር የምንጣደፍበት ምክንያት አይታየኝም። እኛ በዚህ አጀንዳ ላይ ለመወያየት ዝግጁ ባለመሆናችን ውይይቱ እንዲቋረጥ እጠይቃለሁ” ሲሉ የፓርላማ አባላቱ በሙሉ ጭብጨባ ደግፈዋቸዋል።
አቶ ሽመልስ የተባሉ የኦህዴድ አመራር አባል ለውይይቱ ዝግጁ አይደለንም፣ ህዝቡ ሳይወያይበት ዛሬ አጽድቀነው ነገ እንዴት ልንተገብረው ነው? ምክር ቤቱስ ሕዝቡ ያልተወያየበትን ለማጽደቅ እኛን ብቻ የሚጠራው ከምን አንጻር ነው? ስለዚህ እንደ ክልላችን ውይይቱን በሌላ ጊዜ ማድረግ ስለምንችል ስብሰባው እንዲበተን እጠይቃለሁ ሲሉ ሌላ ጭብጨባ አጅቧቸዋል።
ዶ/ር ግርማ መኮንን በምክር ቤቱ የአባላት የአሰራር ደንብ ላይ ሕዝቡ የራሱን አስተያየት ሳይሰጥበት እዚህ መጥቶ መወያየቱ ለምን አስፈለገ? ቋሚ ኮሚቴው ይህን ስራ ሳይሰራ ይህን ውይይት መጥራቱ ለምን አስፈለገ? የምን ሱሪ በአንገት ነው? ብለው አስተያየት ሲሰጡ ሌሎች አባላት በጭብጨባ አጅበዋቸዋል።
አቶ አባዱላ ገመዳ፣ ውይይቱ ቢደረግ ጥሩ ነው ምንም ክፋት የለውም፣ ሲሉ ተሰብሳቢዎቹ በአንድ ድምጽ በግድ ነው? የደርግ ስርዓት ነው የምታራምዱት? በማለት በጩኸት አቋርጧቸዋል። የህወሃቱ አቶ አስመላሽ ወ/ስላሴም ስብሰባው ቢደረግ ይሻላል ሲሉ ተሰብሳቢው በሙሉ ደምጽ “አናደርግም ካልን አናደርግም ነው” ብሎ ሲነሳ፣ “የሻይ እረፍት እናድርግ” ተብሎ እንዲቋረጥ ተደርጓል።
አባ ዱላ የኦህአዴድን የፓርላማ አባላቱ ለብቻ በመጥራት ሊያግባቡዋቸው ቢሞክሩም ሳይችሉ ቀርቷል። ከሻሂ እረፍት እንደተመለሱ ስብሰባው እንዲበተን ተደርጓል።
የፓርላማ አባለት በቅርቡ በኦሮምያ ውስጥ የሚፈጸመውን ግድያና መፈናቀል በተመለከተ የአገሪቱ ጠ/ሚኒስትር ማብራሪያ እንዲሰጡዋቸው ካልሰጡዋቸው ግን በስብሰባ ለመገኘት ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ገልጸው ነበር።

No comments:

Post a Comment