Tuesday, December 19, 2017

ህወሃት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሄዱትን ተቃውሞዎች እንደሚቆጣጠራቸውና አባላቱ እንዲረጋጉ መከረ

 ታህሳስ 8 ቀን 2010ዓም ሃረር ከተማ ላይ በተደረገው የህወሃት ስብሰባ ላይ ጡረታ የወጡ፣ በቦርድ የተገሉና በስራ ላይ ያሉ ወታደራዊ አዛዦች ፣ ነባር አመራሮችና የድርጅቱ ነባር አባላት የተገኙ ሲሆን፣ ሰብሳቢው የህወሃት ቅስቀሳና ፕሮፓጋንዳ ክፍል ውስጥ የሚሰሩት አቶ ዘላለም ለገሰ፣ አባሎች እንዲረጋጉ መክረዋል።
አቶ ዘላለም “ እኛ በሰጠነው ጅራፍ እኛው እየተገረፍን ነው፣ እኛ ስልጣን ሰጥተን መልሰው እኛ ላይ ዞረውብናል፣ መስዋትነት መክፈል የህወሃት የተለመደ ባህሪው በመሆኑ፣ የተወሰነ መስዋት የምንከፍል ቢሆንም፣ ድል እናደርጋለን” በማለት ለአባላቱ ተናግረዋል።
“ምንም ከቁጥጥራችን ስር የሚወጣ ነገር የለም” ያሉት አቶ ዘለላም፣ ኦህዴድና ብአዴንን በእብድነት መስለዋቸዋል። “ሁለቱም ድርጅቶች ያበዱ ስለሆኑ እኛ ከአበዱት ጋር አናብድም፣ ነገር ግን አጥፊዎችን ለፍርድ ለማቅረብ እየሰራን ነው” ብለዋል። አባላቱና ደጋፊዎቻቸው እንደ ድሮው በይፋ እንዳይጋፈጡ፣ በስውር እንዲታገሉ፣ በስውር መረጃ እንዲሰጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ከዚህ በሁዋላ ፊት ለፊት መታዬት አደጋ የሚያመጣ መሆኑንም
ገልጸዋል።
በአገሪቱ የሚታዬውን ተቃውሞ በሃይል እና በህግ እንደሚቆጠጠሩት የዛቱት ባለስልጣኑ፣ ከተሰብሳቢዎች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች መልሶችን ሰጥተዋል። ጥያቄዎች በሙሉ በትግራይ ተወላጆች ደህንነት እና በህወሃት የወደፊት እርምጃ ዙሪያ ያተኮሩ ነበሩ።
አሁን የሚደረገውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ አስመልክቶ የህወሃት ከፍተኛ ባለስልጣናት የማረጊያ መግለጫዎችን እየሰጡ ነው። አዲሱ የህወሃት ሊ/መንበር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል የህወሃት ንብረት ከሆነው ፋና ሬዲዮ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ፣ አሁን የሚታየውን ተቃውሞ ለመቆጣጠር ህወሃት የተለመደ መስዋትነት እንደሚከፍል ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment