Wednesday, December 27, 2017

የዘይትና ስኳር እጥረቱ ተባብሶ ቀጥሎአል

በአማራ ክልል ከሚሴ ከተማ ከአረብ ሀገር ተመልሰው በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው እንዲሰሩ የተደረጉ ዜጎች፣ የዘይትና ስኳር እጥረት ከሚፈጥረው ችግር በተጨማሪ በሚጣልባቸው የተጋነነ ግብርና የመስሪያ ዕቃ አቅርቦት ችግር ሥራቸውን መስራት እንዳልቻሉ ተናግረዋል። 
በምግብና ሻይ ቤት የንግድ ስራ የተሰማሩ ቅሬታ አቅራቢዎች እንደሚናገሩት ባለፈው ዓመት ጀምሮ የተከሰተው የስኳርና ዘይት እጥረት ችግር መፍትሄ ሳያገኝ ከስድስት ወራት በላይ በመቀጠሉ ሥራቸውን በአግባቡ መስራት ተስኗቸዋል፡፡
አንድ ኪሎ ስኳር 35 እና 40 ብር በመግዛት ይገለገሉ እነደነበር የሚገልጹት ቅሬታ አቅራቢ፤ በዚህ ዓመት በሃምሳ እና ስልሳ ብር ለአንድ ኪሎ ስኳር በመክፈል እየተገለገሉ ነው፡፡ ዘይትም ከሃያ ስድስት ብር ወደ ሰባ እና ሰማኒያ ብር መግባቱም ለስራቸው ትልቅ እንቅፋት በመፍጠር እንዲቸገሩ ማድረጉን ይናገራሉ፡፡

ችግር እንደ ደረሰባቸው የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ ዘይትና ስኳር አቅርቦት ሳይኖር እና ያለስራ ቢቆዩም ለአንድ “ኮንቴይነር” ከአስር እስከ አስራ አምስት ሽህ ብር ግብር በመጠየቃቸው ተበድረው ለመክፈል የተገደዱ ከአረበ ሃገር ተመላሾች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡ሥራ ሰርተን በመለወጥ ቤተሰቦቻችንን እናግዛለን በማለት ተደራጅተው ቢንቀሳቀሱም የገዥው መንግስት አመራሮች በህብረተሰቡ ዘንድ በየቀኑ አስፈላጊ የሆኑትን ስኳርና ዘይት የመሳሰሉ አቅርቦቶች ባለሟሟላቱ አብዛኞች በጥቃቅን እና አነስተኛ የተደራጁ ምሩቅ ወጣቶችና ከስደት ተመላሾች ተስፋ ቆርጠው ሥራውን ለመተው እንዲገደዱ አድረጓቸዋል፡፡
አንድ ኩንታል ከሰል በ350፣ስኳር በ50 እና በ60 ብር ገዝተው በመነገድ ለውጥ ለመምጣት እንደመይችሉ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢ ይህ ችግር ባለበት ሁኔታ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁትን በተለዬ ሁኔታ ከማየት ይልቅ እንደ ከፍተኛ ባለሃብቶች ግብር መጣሉ አግባብ እንዳልሆነ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለስድስት ወራት ምንም ዓይነት ስራ ሳይሰሩ ወለድ እንዲከፍሉ መገደዳቸውን በሰቆጣ ከተማ በቴክኒክና ሙያ የተደራጁ ምሩቅ ወጣቶች ተናግረዋል፡፡ ምሩቆቹ በደሮ ማርባት ስራ ለመሰማራት አንድ መቶ ሃምሳ ሽህ ብር በብድር ቢወስዱም፣ ለዶሮ ጫጭቶች አስፈላጊ የሆነው የመብራት አገልግሎት እና ለጫጩት ቀለብ የሚሆን ምግብ ባለመኖሩ ስራቸውን መጀመር አልቻሉም፡፡በተመረቁበት የትምህርት ዓይነት በግላቸው ተወዳድረው ስራ ለማግኘት እንዳይችሉ በዕዳ መያዛቸውን እንቅፋት አንደሆነባቸው የሚገልጹት ወጣቶችም ምንም ሥራ ሳይሰሩ ወለዱን ከኪሳቸው ከፋይ መሆናቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል፡፡
የገዥው መንግስት ለወጣቶች የስራ ዕድል እየፈጠረኩ ነው ቢልም ወጣቱ ሰርቶ እንዲለወጥ ሳይሆን ባለዕዳ በመሆን ተመልሶ የቤተሰብ ሸክም እንዲሆን እየተደረገ መሆኑ ለዜጎቹ የማያስብ አመራር በየቦታው እንዳለ ማሳያ መሆኑን ወጣት ምሩቃኑ አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment