Friday, December 1, 2017

በአዳማ በፖሊስ በጥይት የተደበደቡት አቶ ወርዶፋ ህይወታቸው አስጊ ሁኔታ ውስጥ ነው

በአዳማ ከተማ ረቡእ እለት ህዳር 20 ቀን 2010 ዓ.ም ቦኮ ሚካኤል በመባል በሚጠራው አካባቢ የአርሶ አደሮችን መሬት በሊዝ ለመቀራመትና ታስቦ መኖሪያ ቤቶችን ለማፍረስ በተደረገ ሙከራ የአካባቢው ነዋሪዎችን አመጽ በመደገፍ የሃዋስ መሰናዶ ትምህርት ቤት ተማሪዎች አድማውን መቀላቀላቸው ይታወሳል።
በእለቱ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ ተቃውሞ ወቅት ''በህይወት እያለሁ መኖሪያ ቤቴን አታፈርሱም'' በማለት በመቃወማቸው በፖሊስ በሶስት ጥይት በጭካኔ ተደብድበው ሆስፒታል የገቡት አቶ ወርዶፋ በአሁኑ ወቅት ኮማ ውስጥ መግባታቸውን ምንጮቻችን ገልጸዋል። አቶ ወርዶፋ እስካሁን ከቤተሰብ ውጪ ከፍተኛ ሕክምና እንዲያገኙ ጥረት አልተደረገም።
በእለቱ በተቀሰቀሰው ተቃውሞ በከተማዋ አሰላ መንገድ በመባል የሚጠራው ወደ አርሲ የሚወስደው ዋና መንገድ መዘጋቱን ተከትሎ የአንድ የነጋዴ ስኳር የጫነ ከባድ መኪና ከነተሳቢው ሙሉ ስኳሩ በነዋሪዎች ተዘርፏል። በወቅቱ ሹፌሩ እራሱን በማትረፍ ያመለጠ ሲሆን በሥፍራው የነበሩ ታጣቂዎች ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ ተቆጥበዋል።

የተቃውሞው ቀን ረቡእ የከብት ገበያ ቀን በመሆኑ በተኩስ ልውውጥ ምክንያት ከስድስት በላይ በሬዎች ሲገደሉ ሲሆን ቁጥራቸው ከ200 በላይ የሚሆኑ የነጋዴ ሰንጋዎች ተዘርፈዋል። በተጨማሪም የሃዋስ መሰናዶ ትምህርት ቤት መስኮት መስታወቶች በተቃዋሚዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።
ከከተማዋ መውጫ ከሉጎ ገበሬ ማኅበር ጀምሮ እስከ አዋሽ መልካሳ መዳረሻ ያሉትን አርሶ አደሮች አፈናቅሎ መሬቱን በሊዝ ስም በሙስና ለመቀራመት መስተዳደሩ ከሚያደርገው ድርጊት ካልታቀበ የብዙ ዜጎች ሕልውና አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል ሲሉ ምንጮቻችን ስጋታቸውን ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment