Thursday, October 29, 2015

10 የፌ. ፖሊስ አባላት ኮንሶና ቦረና መገንጠያ ድልድይ ላይ ከነመኪናቸው ተደመሰሱ ሲል አርበኞች ግንቦት 7 ድምጽ ዘገበ


እንደ ራድዮው ዘገባ በትናንትናው ዕለት አመሻሽ ላይ አስሩ የፌደራል ፖሊሶች መጀመሪያ አንድ አይሱዙ የጭነት መኪና በኃይል በማስገደድ አስቁመው የተሳፈሩ ሲሆን መኪናው መንቀሳቀስ ሲጀምር “የጫንካቸውን ፖሊሶች አራግፍ አለያ ከነንብረትህ አብረህ ትጋያለህ!” የሚል የስልክ ማስጠንቀቂያ መልዕክት ለአሽከርካሪው በመድረሱ አሽከርካሪው መኪናውን አቁሞ ፖሊሶቹን “አልሄድም” ይላቸዋል፡፡ ቀጥሎም ፌደራል ፖሊሶቹ ሾፌሩን ለማንገራገር ሞክረው ትዕዛዛቸውን በቀላሉ ሊቀበል ባለመቻሉ ስልክ ተደዋውለው ሌላ ላንድ ክሩዘር መኪና እንዲመጣላቸው በማድረግ ተሳፍረው ጉዟቸውን ቀጥለው ኮንሶ እና ቦረና መገንጠያ ድልድይ ላይ ሲደርሱ ቅፅበታዊ ጥቃት ተከፍቶባቸው ከነተሳፈሩበት መኪና ሙሉ በሙሉ ተደምስሰዋል ብሏል የአርበኞች ግንቦት 7 ድምጽ:: ራድዮው ዘገባውን በመቀጠል የአርባ ምንጭ ከተማ ከፍተኛ ቁጥር ባለው የልዩ ኃይል እና የፌደራል ፖሊስ ጦር ተወራ ጓዳ ጎድጓዳዋ ሳይቀር እየታሰሰ ነው ብሏል:: ራድዮው እንደሚልው እየተፋፋመ ያለው የፀረ-ወያኔ ትግል እየተካሄደባቸው ከሚገኙት የደቡብ ኢትዮጵያ ከተሞች አንዷ አርባ ምንጭ መሆኗ እና በህወሓት የደህንነት ተቋም ጥርስ ውስጥ ገብታ አገዛዙ በአዓይነ ቁራኛ እየተከታተላት የምትገኝ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ከሰሞኑ ደግሞ አርበኞች ግንቦት 7 አንድ አይሱዙ ሙሉ የጦር መሳሪያ ወደ ከተማዋ አስገብቷል በሚል የህወሓት ልዩ ኃይሎች፣ ፌደራል ፖሊሶችና ደህንነቶች በየመንደሩ ተሰራጭተው ከፍተኛ አሰሳ እያደረጉ የነዋሪዎችን የዕለት ተዕለት የህይወት እንቅስቃሴና ሰላም በማወክ ላይ ናቸው፡፡ በተያያዘ ዜና ሙሉጌታ አባ፣ ፀጋዬ ገብረ ፃድቅ እና በኃይሉ ሲሳይ የተባሉ የህወሓት ጆሮ ጠቢዎችና የአካባቢው ቆራጭ ፈላጮች ፎቶግራፋቸው በማህበራዊ ሚዲያው መሰራጨቱን ተከትሎ ከትናንት ምሽት ጀምሮ አርባ ምንጭ ከተማ ከከዚህ ቀደሙ በባሰ ሁኔታ በፌደራል ፖሊስ ተጥለቅልቃ እየታመሰች ትገኛለች ሲል ራድዮው ዘግቧል:: ይህን ዜና የሚያስተባብል መረጃ ከመንግስት በኩል እስካሁን የተሰጠ ነገር የለም:: ዘ-ሐበሻ ተጨማሪ መረጃዎችን ለማግኘት ያደረገችው ሙከራም አልተሳካም::

No comments:

Post a Comment