Thursday, October 15, 2015

መንግስት ለመከላከያ ሰራዊት ምዝገባ አዲስ ቅስቀሳ ጀመረ

ጥቅምት ፬ (አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ካለፈው አመት ጀምሮ እንደ አዲስ በተጀመረው የሰራዊት ምልመላ የተፈለገውን የሰራዊት ቁጥር ማግኘት የተቸገረው መንግስት፣ ሰሞኑን ደግሞ በአንዳንድ ክልሎች የመከላከያ ሰራዊት አባላት በመኪና ላይ ሆነው ወጣቱ ለውትድርና እንደሚዘገብ በመቀስቀስ ላይ ናቸው።

ከዚህ ቀደም ለእያንዳንዱ ቀበሌና ወረዳ የተሰጠው ኮታ ሊሟላ ባለመቻሉ፣ መንግስት በስራ ስልጠና ስም ወጣቶችን በመቀስቀስ ያለፍላጎታቸው እንዲዘምቱ ለማግባባት ሙከራ አድርጓል። ይሁን እንጅ መረጃው በሚዲያ መለቀቁን ተከትሎ፣ ወጣቶች በስራ ስልጠና ስም የሚደረገውን ቅስቀሳ ባለመቀበላቸው አብዛኞቹ ወታደራዊ ማሰልጠኛዎች ሰው አልባ ሆነው ቆይተዋል።
ሰሞኑን በኦሮምያና በደቡብ የመከላከያ ሰራዊት አባል መንግስት የስራ እድል ፈጥሮላችሁዋል እና ተመዝገቡ በማለት በመቀስቀስ ላይ ሲሆኑ፣ ህዝቡ ” የስራ እድል ተፈጥሯል” በሚል ለሚቀርበው ቅስቀሳ የሚሰጠው መልስ ፌዝ ብቻ ሆኗል ሲል የደቡብ ተወካይ ጠቅሷል።

በሌላ በኩል ደግሞ አርበኞች ግንቦትን የሚያወድሱ መፈክሮች በአርባምንጭ ከተማ ግድግዳዎች ላይ ተጽፈው በማደራቸው እንዲሁም የተለያዩ በራሪ ወረቀቶች በመበተናቸው፣ በከተማዋ ፖሊስ ጥበቃውንና ክትትሉን አጠናክሮ ውሎአል።
” ድል ለአርበኞች ግንቦት7፣ ሞት ለወያኔ” የሚሉትን ጽሁፎች ፖሊሶች ሲያጠፉ የሚያሳዩ የፎቶ ማስረጃዎች ደርሰውናል። ተመሳሳይ በራሪ ወረቀቶች በባህርዳርና ጎንደር ከተሞች ተሰራጭተው ነበር።
በአንዳንድ የአገሪቱ ከተሞች ወጣቶች መፈክሮችን በመጻፍ ተቃውሞአቸውን ሲገልጹ፣ በቴፒ ደግሞ ወጣቶቹ ተደጋጋሚ ጥቃቶችን እየፈጸሙ ነው። ሰሞኑን በፖሊስ እና በኢህአዴግ ካድሬዎች ላይ የወሰዱት እርምጃ እንዳለ ሆኖ፣ ወጣቶቹ ከሁለት ቀናት በፊት ደግሞ የሁለት ድርጅት ዘበኞችን መሳሪያዎች ነጥቀው መሰወራቸውን ምንጮች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment