Friday, October 16, 2015

የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የዋጋ ንረቱን እያባባሰው ነው ተባለ

ጥቅምት ፭ (አምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአገሪቱ የሚታየው የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት እጥረት ካለፉት ስድስት ወራት ወዲህ ለታየው አጠቃላይ የዋጋ ንረት መባባስ አንድ ምክንያት መሆኑን ከንግድ ሚኒስቴር የተገኘ አንድ የጥናት ሰነድ ጠቆመ፡፡

በምግብ ነክ ምርቶች ላይ ማለትም በምግብ ዘይት፣ ዱቄት፣ ፓስታና ሞኮረኒ፣ በዳቦ ምርቶች ላይ የተሰማሩ አነስተኛና መካከለኛ አንዱስትሪዎች በኤሌክትሪክ እጥረት ምክንያት ከማማረት አቅማቸው በታች ለማምረት በመገደዳቸው በገበያ ላይ የምርት እጥረት አጋጥሞአል፡፡ በዚህም ምክንያት ሁሉም ዓይነት ምርቶች ላይ የዋጋ ጭማሪ መከሰቱን ጥናቱ ጠቁሞአል፡፡
ከዚህም ችግር ጋር ተያይዞ እንደምግብ ቤቶች ያሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማትም ሙሉ ጊዜያቸውን በስራ ላይ ማሳለፍ ባለመቻላቸው በተመሳሳይ ሁኔታ ዋጋቸው ላይ ጭማሪ ለማድረግ ተገድደዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ መረጋጋት የትራንስፖርት ዋጋ እንዲረጋጋ ያደረገ ቢሆንም፣ ከክልሎች ተጓጉዘው ለአዲስአበባ ገበያ የሚቀርቡ እንደምስር፣ ሽንኩርት፣ ቲማቲም፣ ጎመን፣ ቃሪያና የመሳሰሉ ምርቶችም ላይ የዋጋ ጭማሪው በከፍተኛ ደረጃ መንጸባረቁ ታውቆአል፡፡ የአሁኑ የዋጋ ንረት ሁለንም ዘርፎች የሚነካ መሆኑ ሲታይ በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ጫና ያስከተለ መሆኑን መረዳት ይቻላል ያለው ይህ ጥናት ፣ መንግስት ችግሩ መኖሩን ቢያውቅም ህዝቡን ግን ለመታደግ አቅም አጥሮት ታይቶአል ሲል ይተቻል፡፡

በሌላ ዜና የማዕከላዊ ስታስቲክስ ባወጣው መግለጫ የዋጋ ግሽበቱ ተባብሶ በነሀሴ ወር ከነበረበት 11 ነጥብ 6 በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም ወደ 11 ነጥብ 9 ከፍ ማለቱን አሳውቆአል፡፡ የዋጋ ንረቱ በተለይም በምግብ ምርቶች ማለትም በስጋና የወተት ተዋኖኦዎች፣ እንቁላል እንዲሁም ዘይትና ጥራጥሬዎች ላይ ጎልቶ መታየቱን ጠቁሞአል፡፡
ሸማቾች እንደሚሉት ደግሞ አንድ ኪሎ በርበሬ አምና ከነበረበት 45 ብር ዘንድሮ በኪሎ 195 ብር መግባቱ በደሃው ህዝብ ኑሮ ላይ ከፍተኛ ተጽኖ አምጥቷል። በዘንድሮው የምርት አመት የታየው ዝናብ እጥረት በሚቀጥሉት ወራት ያለውን የእህል ገበያ ዋጋ ሊያንረው ይችላል የሚል ስጋትም አለ።
በተመሳሳይ ዜና በባህርዳር ከተማና በዙሪያዋ ቀበሌዎች የሚገኙ ነዋሪዎች ሰሞኑን ቅጥባጣው የኤሌትሪክ አቅርቦት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ በጋራዥ፣በእንጨት፣በካፌ፣በምግብ እና በቡሎኬት ማምረት ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች በቀን ከአምስት ጊዜ በላይ የኤሌትሪክ መቆራረጥ በመከሰቱ በስራቸው ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማሳደሩን ለዘጋቢያችን ገልጸዋል፡፡
በከተማዋ ከወትሮው በባሰ ሁኔታ የሚታየው የኤሌትሪክ መቆራረጥና የኃይል መብዛት የተለያዩ በኤሌትሪክ የሚሰሩ ዕቃዎቻቸውን እንዳቃጠለባቸው የሚናገሩት ነዋሪዎች፣ መስሪያ ቤቱ ለተቃጠሉት እቃዎች ተገቢውን ካሳ ከመክፈል ይልቅ የተለያየ ምክንያት በመፍጠር ካሳ ለመስጠት ፈቃደኛ እንዳልሆነ ገልጸዋል፡፡
በአዲሱ አመት መግቢያ ማግስት የስራ እንቅስቃሴ ቀዝቀዝ እንዳለ የሚናገሩት የጋራዥ ባለንብረቶች፣ የኤሌትሪኩ መቆራረጥ በእንቅርት ላይ ጆሮ ገድፍ እንደሆነባቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment