Friday, October 9, 2015

በመጪው ወር የሚጠበቀው ከፍተኛ ዝናብ ተጨማሪ አደጋ ደቅኗል

መስከረም ፳፰ (ኅያ ስምት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ የተከሰተውና ከ4 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሕዝብ ለምግብ እጥረት የዳረገው የድርቅ ችግር በቀጣይ ወራትም ሊስፋፋ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።

ከብሔራዊ ሚቲሮዎሎጂ ኤጀንሲ የወጡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከኤልኒኖ ክስተት ጋር ተያይዞ ከቀጣይ ጥቅምት ወር ጀምሮ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በአብዛኛው የሀገሪቱ ክፍሎች እንደሚያጋጥም ዓለም አቀፍ ትንበያ መኖሩን በመጥቀስ፣ ይህ ሁኔታ ድርቁ በሌሎች አካባቢዎች እንዲሰፋ የራሱ ተዕእኖ እንደሚኖረው ተገምቶአል፡፡
በትንበያው መሰረት ከጥቅምት ወር 2008 ጀምሮ በትግራይ፣ በአማራ ክልል -በባህርዳር ዙሪያ፣ በደቡብና ሰሜን ጎንደር፣ ደቡብና ሰሜን ወሎ ፣ በኦሮሚያ ክልል- በኢሉአባቦራ እና ጅማ፣ምዕራብና ምስራቅ ወለጋ፣ ሐረሪ፣ ድሬዳዋ፣ አዲስ አበባ፣ በአፋር ከልል፣ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል- በጋምቤላ ፣ በደቡብ ክልል- በከፋና ቤንች ማጂ ዞኖች መደበኛና ከመደበኛ በላይ ዝናብ እንደሚያገኙ ታውቆአል፡፡

ይህ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በእነዚህ የድርቅ ተጎጂ አካባቢዎች መከሰቱ ሰብሎችን ከማውደሙ ባሻገር የውሃ ወለድ በሽታዎች እንዲከሰቱ በማድረግ ማህባራዊ ቀውሱን ጠቁሞአል፡፡
በቀጣይ ወራት በሁሉም የሀገሪቱ ክፍሎች የችግሩ መስፋት አዝማማያ መኖሩ ችግሩ ከአቅማችን በላይ አይደለም በማለት በተደጋጋሚ የተናገረውን ኢህአዴግ መራሹን መንግስትን
ከባድ ስጋት ላይ ጥሎታል፡፡
ከግብርና ሚኒስቴር በተገኘ መረጃ መሰረት ዘንድሮ በምግብ እጥረት ከተጠቁ አካባቢዎች የኦሮሚያ ክልል በ40 በመቶ ትልቁን ድርሻ ይዞአል፡፡ ቀሪዎቹ ተጠቂ ቦታዎች ደግሞ አማራ 13 በመቶ፣ ትግራይ 9 በመቶ፣ ሶማሌ 4 በመቶ ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ በደቡብ፣ አፋር፣ ሐረሪና ድሬዳዋ የሚገኙ መሆናቸው ተረጋግጦአል፡፡

No comments:

Post a Comment