Thursday, October 29, 2015

እነ ሀብታሙ አያሌው ለጥቅምት 22 ተቀጠሩ

᎐ማረሚያ ቤት እነ ሀብታሙን አላቀረባቸውም
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
የሽብርተኝነት ክስ ተመስርቶባቸው በፌደራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት መከላከል ሳያስፈልጋቸው በነጻ እንዲሰናበቱ የተበየነላቸው የአንድነት፣ የሰማያዊ እና የአረና ፓርቲዎች አመራሮች ላይ አቃቤ ህግ ይግባኝ ጠይቆ ጉዳያቸው በጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙት አምስት ተከሳሾች ለጥቅምት 22/2008 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡ 
ዛሬ ጥቅምት 17/2008 ዓ.ም የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ ተብሎ ቢጠበቅም ማረሚያ ቤት ሳያቀርባቸው በሌሉበት ቀጠሮ የተሰጣቸው የፓርቲዎች አመራሮቹ ሀብታሙ አያሌው፣ የሺዋስ አሰፋ፣ አብርሃ ደስታ፣ ዳንኤል ሺበሽ እና አብሯቸው ይግባኝ የተጠየቀበት አብርሃም ሰለሞን ናቸው፡፡ 
የቂሊንጦ እና የቃሊቲ ማረሚያ ቤቶች እነ ሀብታሙን ፍርድ ቤት ያላቀረቡበትን ምክንያት ፍርድ ቤቱ ሲጠይቅ፣ ‹‹ቃሊቲ በፕላዝማ ይታያል ስለተባለ አላመጣናቸውም፤ ከአይ.ሲ.ቲ ጋር ተነጋግረው ነው ያስቀሯቸው›› የሚል መልስ ተሰጥቷል፡፡ ማረሚያ ቤቱ እነ ሀብታሙን ብቻ ሳይሆን በሌላ መዝገብ በተለያዩ ወንጀሎች ስር የተጠቀሱ ተከሳሾችንም አለማቅረቡ ታውቋል፡፡
ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የቃሊቲ ማረሚያ ቤትን መልስ ካደመጠ በኋላ፣ ‹‹ይሄ ቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚባል ነገር የሚሆን አይደለም፤ አቅርቧቸው ብለን አዝዘን ነበር፤ እኛ ነን የምናዝዛችሁ ወይስ ማን ነው? አሁንም ቀጣይ ቀጠሮ ላይ አቅርቧቸው›› ሲል በእነ ሀብታሙ መዝገብም በሌሎች መዝገቦችም ላይ ዛሬ ላልቀረቡ ተከሳሾች ተመሳሳይ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ በመሆኑም እነ ሀብታሙ አያሌው ሰኞ ጥቅምት 22/2008 ዓ.ም የተጠየቀባቸው ይግባኝ ያስቀርባል ወይስ አያስቀርብም የሚለውን ብይን ቀርበው ለመስማት ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment