Tuesday, October 13, 2015

ህወሃት ያገለላቸውን የቀድሞ አባላቱን እየመለሰ ነው ተባለ

ኢሳት ዜና (ጥቅምት 2 ፣ 2015)

የህዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሐት ) ማእከላዊ ኮሚቴ ከአመታት በፊት በጡረታ የተገለሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች በድጋሚ እንዲደራጁ አዘዘ።
ባለፈው እሁድ በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመቀሌ ከተማ ጉባኤ ያካሄደው የህወሀት ማእከላዊ ኮሚቴ፣ በትጥቅ ትግሉ ወቅት እንዲሁም በጡረታ ሰበብ የተሰናበቱ ታጋዮች ዳግም የማደራጀት ስራ እንዲካሄድ ወስኗል።
ከአመታት በፊት በእድሜና በተለያዩ ምክኒያቶች በሺዎች የሚቆጠሩ የህወሀት ታጋዮች እንዲሰናበቱ ተደርጎ የነበረ ሲሆን፣ እነዚህ ተሰናባች ታጋዮች ድጋሚ ተደራጅተው የተለያዩ ሃላፊነቶችን እንዲወጡ የህወሀት ማእከላዊ ኮሚቴ መወሰኑን ከሀገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል። ይሁንና በድጋሚ እንዲደራጁ  የተደረጉ ታጋዮች ቁጥር በግልጽ አታወቅም።

በነሀሴ ወር መጨረሻ ላይ አመታዊ ጉባኤውን አካሂዶ የነበረው ህወሐት በመተካካት ስም ተሰናብተው የነበሩ የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት በአባልነት እንዲቀጥሉ የተደረገውን ግፊት ውድቅ ማድረጉ ይታወሳል።
የቀድሞ ማእከላዊ ኮሚቴ አባላት እንዲመለሱ የተደረገው ጥረት ከከሽፈ በኋላ በጡረታ እና በተለያዩ ምክኒያቶች የተሰናበቱት በሺዎች የሚቆጠሩ ታጋዮች ድጋሚ እንዲደራጁ ሲደረግ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ታውቋል።
በመንግስት የስልጣን ሀላፊነትን በአብዛኛው ተቆጣጥሮ የሚገኘው ህወሐት /ኢህአዴግ የተሰናበቱ ታጋዮችን በድጋሚ ለማደራጀት ስላስፈለገበት ሁኔታ በቂ ዝርዝር መግለጫን ከመስጠት ተቆጥቧል።
በህወሐት ማእከላዊ  ኮሚቴ አባልነትና በተራ አባልነት የታቀፉ በርካታ ግለሰቦች በተለያዩ የመንግስት ተቋማት ውስጥ በሀላፊነት እያገለገሉ እንደሚገኙ ይነገራል።

No comments:

Post a Comment