Wednesday, October 21, 2015

አቶ አበበ ካሴ በማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈፀመበት እንደሆነ ገለፀ።

ኢሳት ዜና:-በሽብርተኝነት ተከሶ በቂሊንጦ ማረሚያ ቤት የሚገኘው አቶ አበበ ካሴ እስር ቤት ውስጥ በማንነቱ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየደረሰብኝ ነው ሲል ለፍርድ ቤቱ አቤቱታውን አሰምቷል፡፡ በእነ አበበ ካሴ የክስ መዝገብ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነው አቶ ታጠቅ አስማረ የተከላካይ ጠበቃ ለማቅረብ ዛሬ ጥቅምት 9/2008 ዓ.ም ፍርድ ቤት በቀረበበት ወቅት ለልደታ ፍርድ ቤት 19ኛው ወንጀል ችሎት አቤቱታውን ያቀረበው አቶ አበበ ካሴ በማረሚያ ቤቱ በተደጋጋሚ የሰብአዊ መብት ጥሰት እየተፈፀመበት እንደሚገኝና ፍርድ ቤቱ መፍትሄ መስጠት እንዳልቻለ ገልፆአል፡፡

‹‹የሥርዓቱ መሪዎች ፍርድ ቤት ነፃ ነው ይላሉ፡፡ እንደዛ ከሆነ እናንተም መብታችሁን መጠቀም አለባችሁ፡፡ እናንተ ናችሁ ማዘዢያ ቆርጣችሁ የምታሳስሩት፣ የምትፈርዱት፡፡ በመሆኑም ማረሚያ ቤቱን መቆጣጠር አለባችሁ›› ሲል ፍርድ ቤት ግዴታውን እንዲወጣ አሳስቧል፡፡

በርካታ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እንደሚፈፀሙ የገለፀው አቶ አበበ ‹‹ማረሚያ ቤቱ እራሱ ቀበቶ ይሸጣል፡፡ ግን ቀበቶ ይከለክላል፡፡ ለምን ብለን ስንከለክል ሱሪያችሁን መፍታታችሁን እንድታውቁት ይለናል፡፡ በተለይ እኔ በማንነቴ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እየተፈፀመብን ነው›› ብሏል፡፡
ለፍርድ ቤቱ በተደጋጋሚ አቤቱታውን ቢያሰማም የመጣ ለውጥ እንደሌለና አሁንም ማረሚያ ቤቱ ከፍተኛ የመብት ጥሰት እየፈፀመብን ነው ያለው አቶ አበበ ‹‹እናንተ ግዴታችሁን ተወጡ፡፡ ስለ ስርዓቱ ብዙም ነገር አልልም፡፡ በእርግጠኝነት ስርዓቱ ይወድቃል!…›› ሲል ፍርድ ቤቱ ንግግሩን አቋርጦታል፡፡ አቶ አበበ ጠበቃ የሌለው በመሆኑ ቅሬታውን በፅሁፍ እንዲያቀርብ ሲጠየቅም ‹‹ስርዓቱ ወረቀት አይወድም፡፡ ወረቀት ከእስር ቤት አያስወጡኝም፡፡›› በማለቱ ፍርድ ቤቱ የአቶ አበበን ቅሬታ ተቀብሎ እንዲያመጣ ለማረሚያ ቤቱ ጉዳይ አስፈፃሚ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ አቶ አበበ በማእከላዊ እስር ቤት ጥፍሮቹ ተነቃቅለው እንዲሁም በዘር ፍሬው ላይ ከፍተኛ ድብደባ ተፈጽሞበታል።
በተያያዘ ዜና
በኩላሊት ጠጠር በሽታ እየተሰቃየ የሚገኘው የቀድሞው አንድነት የህዝብ ግንኙነት አቶ ሀብታሙ አያሌው ህሙሙ እንደጠናበት ታውቋል፡፡ ዛሬ ጥቅምት 9/2008 ዓ.ም ለመከላከያ ምስክርነት ልደታ ፍርድ ቤት የታየው ሀብታሙ ህመሙ እንደጠናበት ችሎቱን ለተከታተሉት የኢሳት ምንጮች ገልፆአል፡፡ አቶ ሀብታሙ ችሎቱን ቁጭ ብሎ መከታተል ባለመቻሉ ፍርድ ቤቱን አስፈቅዶ ከኋላ ወንበር አካበቢ በተደጋጋሚ እየቆመ እየተቀመጠ ችሎቱን ለመከታተል ቢሞክርም በህመሙምክንያት ባለመቻሉ አስፈቅዶ ከችሎት ለመውጣት ተገድዷል፡፡
አቶ ሀብታሙ በህመሙ ምክንያት ሰኞ ጥቅምት 1 ቀን 2008 ዓ.ም በድንገት ዘውዲቱ ሆስፒታል ገብቶ ለአንድ ቀን እዛው እንዳደረ የሚታወስ ሲሆን ጥቅምት 3 ቀን 2008 ዓ.ም በፌዴራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በነበረው ቀጠሮ ብዙም ሳይሻለውቀርቦ ነበር።
የፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት አቶ ሀብታሙ አያሌውና ሌሎች 3 የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በነፃ እንዲሰናበቱ ወስኖ የነበር ቢሆንም ከእስር እንዳይለቀቁ ተደርገው ይግባኝ ተጠይቆባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ፡፡

No comments:

Post a Comment