Wednesday, October 18, 2017

ኦሮምያ ከተሞች የሚካሄደው ተቃውሞ ቀጥሎ ሲውል የአንድነትና የትብብር ድምጾች ከፍ ብለው እየተሰሙ ነው

(ኢሳት ዜና ጥቅምት 08 ቀን 2010 ዓም) በኦሮምያ ከተሞች የሚካሄደው ተቃውሞ ቀጥሎ ሲውል የአንድነትና የትብብር ድምጾች ከፍ ብለው እየተሰሙ ነው
በተለያዩ የኦሮምያ ከተሞች የሚካሄዱ ተቃውሞዎች ዛሬም ቀጥለው ውለዋል። ሰሞኑን የመከላከያ ሰራዊት አባላት በወሰዱት እርምጃ የተገደለውን ወጣት ፈይሳ አለሙን ለመቅበር የወጣው ህዝብ ተቃውሞውን ወያኔን በማውገዝ አሰምቷል። በአካባቢው ያለውን ውጥረት ተከትሎ ከአዲስ አበባ ወደ ጎጃምና ጎንደር የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ መኪኖች በደብረ ብርሃን ደሴ ዞረው ለመጓዝ ተገደዋል።
በጫንጮ ሰሞኑን ከፍ ብሎ ሲሰማ የነበረው የአንድነን እና የእንተባበር ድምጽ ዛሬም ከፍ ብሎ ይሰማ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል። በመቱ እና በበደሌ ከተማ በነበረው ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴም እንዲሁ ህዝቡ ወያኔ የውደም የሚለውን መፈክር ሲያስተጋባ ውሎአል።
በሱሉልታም በነገው እለት የሚውለውን የገበያ ቀን ተከትሎ የመከላከያ ሲቪል ለባሽ የደህንነት አባላት ቅኝት ሲያደርጉ መዋላቸውን ነዋሪዎች ተናግረዋል።


ዘጋቢያችን እንደገለጸው እስካሁን ድረስ በሚታዬው ተቃውሞ የህዝቡ ጥያቄ በኢትዮጵያ አንድነትና በትብብር ዙሪያ ትኩረት ያደረገ ነው። በህዝቡ ውስጥ የሚታየው አንድነት እየገለበተ መምጣት፣ በህወሃት ደጋፊዎች ላይ ጫና እየፈጠረ መምጣቱንም ዘጋቢያችን ገልጿል። የህወሃት ንብረት የሆኑ አንዳንድ ድርጅቶች እየተሸጡ መሆኑንና ህዝቡ በአንድነት አንገዛም ማለት መጀመሩን በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ የሚገኘውን ሰላም ባስ ለመሸጥ ህወሃት ያወጣው ጫረታ ምላሽ ያጣባትን አጋጣሚ በማንሳት ጠቅሷል። ህወሃት እስካሁን ድረስ መሸጥ የቻለው አንድ አውቶቡስ ብቻ መሆኑን ቀሪዎችን የሚገዛ መጥፋቱን ዘጋቢያችን ገልጿል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከሰሞኑ የሁለት ነባር የኢህአዴግ ባለስልጣናት ስልጣን መልቀቅ የህዝቡ መነጋገሪያ ሆኗል። ኢህአዴግ እየተፈረካከሰ ነው የሚለው ስሜት በህዝቡ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተጋባ ሲሆን፣ በኢህአዴግ ውስጥ የቆየው በፍርሃት ላይ የተመሰረተው መከባበር እያከተመ መምጣቱ ድርጅቱ አደጋ ውስጥ እየወደቀ ነው ብለው የኢህአዴግ አባላት ሳይቀር እየተናገሩ መሆኑን ዘጋቢያችን ገልጿል። ኢህአዴግን በአደባባይ መቃወም ወደ እስር ቤት እንደሚያስወረውር እየታወቀ ፣ በአደባባይ ስላልተደሰትኩ ስራ ለቅቄአለሁ የሚል መግለጫ መስጠት፣ በኢህአዴግ ውስጥ አዛዥና ታዛዥ እየጠፋ መምጣቱን ያሳያል ሲሉም አስተያየት ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment