Monday, July 23, 2018

በባሌ ጎባ አንጻራዊ መረጋጋት ቢታይም አሁንም ስጋቶች እንዳሉ ነዋሪዎች ገለጹ

(ኢሳት ዜና ሃምሌ 16 ቀን 2010 ዓ/ም ) የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት እንደገለጹት ባለፈው ቅዳሜ ደም አፋሳሽ የነበረው ግጭት የመከላከያ ሰራዊት አካባቢውን ከተቆጣጠረው በሁዋላ አንጻራዊ መረጋጋት ታይቶበታል። ባለፈው ረቡዕ የዞኑ ባለስልጣናት የባሌ ገበሬዎች አመጽ መሪ የነበሩትን የሃጂ አደም ሳዶን ሃውልት ለማቆም በሚል ህዝቡን አወያይተው የነበረ ሲሆን፣ በእለቱ አብዛኛው ተሰብሳቢ ሃውልቱ ቢቆም ችግር እንደሌለው ይሁን እንጅ፣ ሃውልቱ በከተማው መሃል አደባባይ ላይ የሚገኘው የቀይ ቀበሮ ሃውልት በሚሰራበት ቦታ ላይ ይሁን መባሉን የተወሰነው የህብረተሰብ ክፍል መቃወሙን የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። አንዳንድ ተሰብሳቢዎች ብዙ ገንዘብ የፈሰሰበትን ሃውልት ከማፍረስ ሌላ ቦታ ላይ መገንባቱ ይሻላል በሚል የተከራከሩ ቢሆንም፣ ባለፈው ቅዳሜ የከተማው ከንቲባን ጨምሮ የዞን አመራሮች ውሳኔውን ለማስፈጸም በመንቀሳቀሳቸው ግጭት ተከስቷል። ግጭቱ ሃይማኖታዊ ቅርጽ እየያዘ መምጣቱን የተናገሩት ነዋሪዎች፣ በተለይም የኦሮምያ ፖሊስ ከሁሉም ጎን ሆኖ ችግሩ እንዳይባባስ ማድረግ ሲገባው፣ በአንድ ወገን ላይ ጥቃት መፈጸሙ እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። የመከላከያ ሰራዊት አባላት ወደ አካባቢው ባይገቡ ኖሮ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ ይችል እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል። የከተማዋ ከንቲባ ዘይነባ ጣሀ ለቢቢሲ አማርኛው ክፍል እንደተናገሩት በግጭቱ የ6 ሰዎች ህይወት ማለፉን እና ብዙዎችም ተጎድተው ህክምና እየተደረገላቸው ነው። የዞኑ አመራሮች ከህብረተሰቡ ጋር ከህብረተሰቡ ጋር በተነጋገሩበት ወቅት በስብሰባው ላይ የተሳተፉት አካላት አብዛኛዎቹ የሐውልቱን መተከል ይቃወሙት ነበር ሲሉ ከንቲባዋ ቢናገሩም፣ በስብሰባው የተሳተፉት
ሌሎች ሰዎች ግን የተቃውሞው መነሻ ሃውልቱ መገንባት አለበት የሌበትም በሚለው ጉዳይ ሳይሆን፣ የቀይ ቀበሮው ሃውልት ፈርሶ ይገንባ በሚለው ጉዳይ ነው በማለት የከንቲባዋን መገልጫ አስተባብለዋል። አብዛኛው ህዝብ በሃውልቱ መገንባት ላይ ቅሬታ እንዳልነበረውና ቅሬታው የቀበሮዎችን ሃውልት ለማፍረስ በተደረገው ሙከራ ላይ ነው ይላሉ። ከገጠር ወደ ከተማ የገቡ እና የተለያዩ የጦር መሳሪያዎችን የያዙ ወጣቶች፣ የቀይ ቀበሮውን ሃውልት አፍርሰዋል። እነዚህ ወጣቶች ወደ መድሃኒያለም ቤተክርስቲያን ባመሩበት ወቅት፣ ቤተክርስቲያኗ የድረሱልኝ ደውል በማሰማቷ፣ ምዕመኑ ቤተክርስቲያኗን ከጥቃት ለመከላከል መውጣቱን ተከትሎ ከኦሮምያ ፖሊስ ጋር ግጭት መፈጠሩን ነዋሪዎች ይገልጻሉ። ከንቲባ ዘይነባ ግን ከገጠር የገቡ ሰዎች ሃውልቱን አፈራርሰው ከከተማዋ እየወጡ እያለ በአቅራቢያው ከሚገኝ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የደወል ድምጽ መሰማቱን፣ የደወል ድምጽ የሰሙ የከተማዋ ናሪዎች ማሳሪያ ታጥቀው መውጣታቸውን ግጭቱ መልኩን መቀየሩን ይናገራሉ። ከዚህ በሁዋላ ከተማዋን ለቅቀው እየወጡ ከነበሩ ሰዎች ጋር ግጭት ተፈጥሮ የሰው ህይወት ማለፉንና ከንቲባዋ ተናግረዋል። ከንቲባዋ ቤተክርስቲያኗን ተጠያቂ ቢያደርጉም፣ ቤተክርስቲያኗ ጥቃት ሊፈጸምባት ሲል ካልሆነ በስቀተር ደወል እንደማትደውልና በእለቱም ቤተክርስቲያኗን የወሰደቸው እርምጃ ራስን የመከላከል እርምጃ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከተማዋ ውስጥ የታጠቁ ኃይሎች እንደነበሩ፣ “ የኦሮሚያ ፖሊስ ከቀኑ 5 ሰዓት ጀምሮ እስከ 12 ሰዓት ድረስ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ሲታኮሰ መዋሉን ሁኔታውን ለመቆጣጠር ግን ከአቅም በላይ እንደነበረበት” ከንቲባዋ ተናግረዋል። ነዋሪዎች ግን የኦሮምያ ፖሊስ ተግባሩን በትክክል አልተወጣም፣ መከላከያ የገባውም ተግባሩን ፍትሃዊ ባልሆነ መንገድ ባለመወጣቱ ነው ይላሉ። የከተማው ነዋሪዎች ከንቲባዋንና የዞኑ አመራሮችን ለችግሩ መነሳት ዋና ታጠያቂዎች ያደርጋሉ።

No comments:

Post a Comment