Monday, July 23, 2018

ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራን ጋር ባደረጉት ዉይይት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባረው የነበሩ መምህራን ወደሥራቸው መመለስ እንደሚችሉ አስታወቁ

(ኢሳት ዜና ሃምሌ 16 ቀን 2010 ዓ/ም )በጠቅላይ ሚኒስቴር የመሰብሰቢያ አዳራሽ ከመላው ኢትዮጵያ ከሃምሳ ዩኒቨርሲቲዎች ከተወጣጡ 3 ሽህ 175 የዩኒቨርሲቲ መምህራን ጋር በአገሪቱ የከፍተኛ የትምህርት ጥራት፣ አገራዊ አንድነት፣ አገሪቱ ስላለችበት ወቅታዊ ሁኔታ፣ ስለ ብልሹ አሰራር እና ሌብነት፣ አጠቃላይ የትምህርት ፖሊሲ፣ ብቃት እና ስነምግባር ያለው ዜጋ ስለማፍራት እንዲሁም ጥናት እና ምርምሮችን በተመለከተ ከጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ጋር ውይይት አድርገዋል። በስብሰባው ላይ የተገኙት መምህራንም ስለ አገሪቱ ወቅታዊ ሁኔታና ስለ መማር ማስተማሩ ተግዳሮቶች አስመልክተው ጥያቄዎቻቸውን አቅርበው ከጠቅላይ ሚንስትሩ ምላሽ ተሰጥቷቸዋል። በትምህርት ጉዳይ አስመልክቶ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መምህርነት የተከበረ ሙያ መሆኑንና በዘርፉ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የጋራ ኃላፊነት መውሰድ ይገባናል። የትምህርት ጥራት ችግር መኖሩን አምነው ይህን ለመቀየር በሠፊው እየሠራን ነው ብለዋል። የመምህራን ደሞዝና ጥቅማጥቅም ዝቅተኛ መሆኑንና ይህንንም ለማሻሻል ከሚመለከተው
አካል ጋር እንወያያለን ብለዋል። የመልካም አስተዳደር እጦትና በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ ግጭቶች በትምህርቱ ዘርፍ ለሚስተዋለው ችግር ዋነኛ ምክንያት መሆናቸውንም ጠቅላይ ሚንስትሩ ጠቁመዋል። ከዚህ ቀደም ተገቢ ባልሆነ መንገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተባረው የነበሩት መምህራን ይቅርታ ተደርጎላቸው ወደ ስራቸው እንዲመለሱ ሲሉ የትምህርት ሚኒስትሩ ጥላዬ ጌጤ ያቀረቡትን ጥያቄ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል። “ይቅርታ መጠየቅ ያለብን እኛ ሆነን ወደ ስራቸው ይመለሱ” በማለት እንዲመለሱ ውሳኔ ሳልፈዋል። ከዛሬ 24 ዓመታት በፊት ከአዲስ አበባ ዩንቨስርቲ የተባረሩ መምህራን መባረራቸው አግባብ አለመሆኑንና በአሁኑ ወቅትም ማስተማር የሚፈልጉ የቀድሞ ተሰናባች ምሁራን ወደ ቀድሞ ሥራቸው መመለስ ከፈለጉ ሊመለሱ ይችላሉ ሲሉ አጽኖት ሰጥተው ተናግረዋል። በጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ሚያዝያ 1985 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ ከተባረሩ አንጋፋ ምሁራን ውስጥ ታዋቂው የልብ ስፔሻሊስት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ ፕሮፌሰር ምንዳርያለው ዘውዴ፣ ዶክተር ፍቃደ ሸዋቀና፣ ዶክተር አድማሱ ገበየሁን ጨምሮ ዓለም አቀፍ እውቅና ያላቸው ነበሩ። ይህን ያህል ቁጥር ያላቸው የዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰሮች በማባረር ኢትዮጵያ በመጥፎ ታሪክ በቀዳሚነት ተርታ ትሰለፋለች።

No comments:

Post a Comment