Thursday, July 5, 2018

ሶስት ግዙፍ የስኳር ፕሮጀክቶች የግንባታ ውሎች ተቋረጡ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 28/2010) የኢትዮጵያ ብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ለዓመታት ሊያጠናቅቃቸው ያልቻላቸው ሦስት ግዙፍ የስኳር ፕሮጀክቶች የግንባታ ውሎች እንዲቋረጡ ተወሰነ።
ውሳኔውን ያሳለፈው የፕሮጀክቱ ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ቦርድ መሆኑ ታወቋል።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም ሜቴክ ከፍተኛ ብክነት እንዳሳየ የታወቀበት የፌደራል ኦዲት ሪፖርት ተይዞ ከቆየ በኋላ ይፋ ተደርጓል።
በፓርላማ የመንግሥት ልማት ድርጅቶች ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የስኳር ኮርፖሬሽኑን ሥራ አፈጻጸም ሰኔ 25 / 2010 ዓ.ም. ሲገመግም ዋና ሥራ አስፈጻሚው አቶ ወንድአወቅ አብቴ ሜቴክ እጁ ላይ የቀሩትን ሦስት ፕሮጀክቶች ለመፈጸም የስድስት ወራት ማራዘሚያ ቢሰጠውም እንዳልጨረሰ ገልጸው ነበር።
እናም ስኳር ኮርፖሬሽኑ በሜቴክ ላይ እምነት እንደሌለው ነበር የገለጹት። አቶ ወንድአወቅ እንዳሉት የስኳር ፕሮጀክቶቹ በአንድ ዓመት ከስድስት ወራት ተጠናቀው ለማስረከብ ታሳቢ ተደርገው የተጀመሩ ነበሩ። በሰባት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግን አንድም ፋብሪካ አልተጠናቀቀም።

የማጠናቀቂያ ጊዜው ከ20 ጊዜ በላይ ተራዝሞለትም ሜቴክ የፈጠረው ነገር እንዳልነበር በመግለጽ የተጠየቀውን ተጨማሪ ጊዜ መፍቀድ ተገቢ ሆኖ እንዳላገኙትም ተናግረዋል።
በመሆኑም የበለስ አንድና ሁለት የስኳር ፋብሪካዎች፣ እንዲሁም የኦሞ ኩራዝ አንድ የስኳር ፋብሪካ ግንባታ ውል እንዲቋረጥ የስኳር ኮርፖሬሽን ማኔጅመንት ወስኖ ለቦርድ እንዳሳወቀና ቦርዱም ውሉ እንዲቋረጥ መወሰኑን አቶ ወንድአወቅ ለቋሚ ኮሚቴው አስታውቀዋል።
‹‹ሁሉም በየፊናው አጨብጭቦ ካደነቀ በኃላ እኛን በየመድረኩ በመገምገም ማስጨነቁ ተገቢ አይደለም፡፡ ኃላፊነት እንወስዳለን፡፡ ነገር ግን ከአቅማችን በላይ ከሆነ ምንም ማድረግ አንችልም፤›› ብለዋል ሜቴክ ከጀመራቸው አሥር ግዙፍ የስኳር ፋብሪካ ፕሮጀክቶች አንዳቸውንም ማጠናቀቅ ሳይችል ተነጥቋል።
የፓርላማው ቋሚ ኮሚቴ ለዕቅዱ አለመሳካት ዋነኛው ምክንያት የአሥሩም ፋብሪካዎች የግንባታ ኮንትራት በዘርፉ ምንም ልምድም ሆነ አቅም ለሌለው የአገር ውስጥ ኩባንያ ሜቴክ መሰጠቱ መሆኑን ይገልጻል።
ከሦስት ዓመት በላይ በዚሁ ጉዳይ ላይ ባደረገው ተደጋጋሚ ግምገማም ይህንኑ መገንዘቡን ሲዘገብ መቆየቱ ይታወሳል።
ከዚህ ቀደም ባሉት ዓመታት መቋረጥ አለባቸው ተብለው በኮርፖሬሽኑ የተገመገሙ የስኳር ፕሮጀክቶችን ውል በማቋረጥ ርምጃ ለመውሰድ የተደረገ ሙከራ ቢኖርም፣ በኮርፖሬሽኑ አመራሮች ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዛቻ በመሰንዘራቸው ርምጃ መውሰድ እንዳልተቻለም አቶ ወንድአወቅ ገልጸዋል።
‹‹ርምጃ ልንወስድ ስንል ይህማ ከግንብ ጋር መጋጨት ነው፡፡ እስኪ ሞክሯትና ወዮላችሁ፤›› እንደተባሉም አጋልጠዋል።
ዛቻውን የሰነዘሩ ባለሥልጣናትን ማንነት ባይገልጹም፣ ጉዳዩ የሚመለከታቸውና ከጉዳዩ ወጪ የሆኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት መሆናቸውን ጠቁመዋል።
በአጠቃላይ የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ከዘጠኝ ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሀብት ማባከኑን ቋሚ ኮሚቴው አስታወቋል።
ይሕ በእንዲህ እንዳለም ሜቴክ ከፍተኛ ብክነት እንዳሳየ የታወቀበት የፌዴራል ኦዲት ሪፖርት ተይዞ ከቆየ በኋላ ይፋ መደረጉ ተገልጿል።
ጉድለቶቹም በጋፋት ኢንጂነሪንግ፥ በአምቦ ሆርማት እና በልዩ ልዩ መጋዘኖች የተከማቹ እቃዎች ለምን እንደተገዙ የማይታወቁ፥ተገዝተዋል ተብለው በተጨባጭ ግን የሌሉ፥ ስለመገዛታቸው መረጃ ያልተገኘባቸው እና የመሳሰሉት ናቸው።
በበርካታ ቢሊዮኖች የሀገር ሃብት እንደባከነ የሚገልጸው የፌዴራል ኦዲት ሪፖርት መጀመሪያ ላይ እንዳይወጣ ተከልክሎ ነበር።
በኋላ ላይ ግን ሪፖርቱ ይፋ እንዲሆን መወሰኑን የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment