Thursday, July 5, 2018

በተለያዩ ድርጅቶች ላይ የተጣለው የሽብርተኝነት ስያሜ ተነሳ

(ኢሳት ዲሲ–ሰኔ 28/2010) በኦሮሞ ነጻነት ግንባር፣በኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባርና በአርበኞች ግንቦት ሰባት ላይ የተጣለው የሽብርተኝነት ስያሜ በይፋ ተነሳ።
በሳምንቱ መጨረሻ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሶስቱ ድርጅቶች ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ እንዲወጡ ያሳለፈውን ውሳኔ ፓርላማው ዛሬ በሙሉ ድምጽ አጽድቆታል።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባደረገው ስብሰባው ከሰባት አመት በፊት በአንድ ተቃውሞ ብቻ የሳለፈውን የአሸባሪነት ስያሜ ዛሬ ላይ በሙሉ ድምጽ ሽሮታል።
ሰኔ 7 ቀን 2003 አመተ ምህረት ሶስት የሃገር ውስጥና ሁለት ድንበር ዘለል ድርጅቶች በአሸባሪነት ሲሰየሙ ብቸኛው የተቃዋሚ ፓርቲ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ ፍረጃውን ተቃውመውት ነበር።

የግል ተመራጭ የነበሩትን ዶክተር አሸብር ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ የኢሕአዴግና የአጋር ፓርቲ አባላት ደግሞ ፍረጃውን ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል።
በዚህ መልክ የዛሬ ሰባት አመት ሰኔ 7 ቀን 2003 አመተ ምህረት በአሸባሪነት የተፈረጁት አርበኞች ግንቦት 7፡ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር /ኦነግ/ና የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር /ኦብነግ/ዛሬ ከአሸባሪነት ዝርዝር ውስጥ እንዲወጡ ፓርላማው በሙሉ ድምጽ ወስኗል።
በአለም አቀፉ አሸባሪ አልቃይዳና በሶማሌው አሸባሪ ቡድን አልሻባብ ላይ የተጣለው የሽብርተኝነት ስያሜ ግን ባለበት ቀጥሏል።
ሶስቱን ሃገር በቀል ድርጅቶች አሸባሪ ብሎ ለመፈረጅ ፓርላማው መነሻ ያደረገው ነሐሴ 22/2001 የታወጀውን የጸረ ሽብር ሕግ እንደሆነም ታውቋል።
በዚህ ሕግና ይህንን ህግ ተከትሎ የፖለቲካ ሃይሎቹ ላይ በተወሰነው ፍረጃ በርካታ የመብት ተሟጋቾች ጋዜጠኞችና ሰላማዊ የፖለቲካ ድርጅት መሪዎችና አባላት ወደ ወህኒ ሲጋዙ መቆየታቸው ይታወሳል።
በዙዎቹም በእስር ቤት ብልታቸውን ከመኮላሸት ጀምሮ የአካል ጉዳት ጭምር እንደደረሰባቸውም ከወህኒ ሲወጡ በሰጡት ምስክርነት መረዳት ተችሏል።

No comments:

Post a Comment