Monday, July 30, 2018

ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ረገጣ ሲፈፀምባቸው የነበሩት አራት የፌደራል ማረሚያ ቤት አመራሮች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደረገ

( ኢሳት ዜና ሃምሌ 23 ቀን 2010 ዓ/ም ) በህግ ጥላ ስር ያሉ ፍርደኛ እስረኞችን በመቀበል የቅጣት ጊዜያቸውን እስኪፈፅሙ ድረስ በማቆያነት የተቋቋሙት ማረሚያ ቤቶች ከፍተኛ የመብት ጥሰት ሲፈፀምባቸው ቆይቷል። ከማእከላዊ ምርመራ ሰቆቃ የተረፍትን ታራሚዎች በመቀበል ኢሰብዓዊ የመብት ጥሰቶች በመፈፀም የሚታወቁት የቂሊንጦ፣ የድሬዳዋ፣ የሸዋሮቢትና የቃልቲ ማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ተነስተው በምትካቸው አዲስ አስተዳዳሪዎች ተሹመዋል። የፌደራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳዳር ዛሬ እንዳስታወቀው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አዛዥ የነበሩት ገ/ኢየሱስ ገ/እግዚአብሔር ተነስተው ኮማንደር ተክሉ ለታ ተተክተዋል። በተመሳሳይ በሸዋ ሮቢት ማረሚያ ቤት አስተዳዳር የነበሩት የማነ አስፋው በኮማንደር እንዳሸው ማሙዬ ተቀይረዋል። የድሬዳዋ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር የነበሩት መኮንን ደለሳ በበኩላቸው በወንድሙ ደበሌ ሲተኩ፤ የቂሊንጦው አስተዳዳሪ አሰፋ ኪዳኔ በኮማንደር ጫላ ጸጋ እንዲተኩ ተደርጓል። የፌደራል ማረሚያ ቤት የኃላፊነት ቦታዎችን ጨምሮ፤ የህክምና ጥበቃና የንብረት አስተዳደር ሹመቶች በአብዛሃኛው በህወሃት የቀድሞ ታጋዮች መያዛቸው ይታወቃል። በቂ መረጃ እያለ እስረኞች ላይ የመብት ጥሰቶች የፈፀሙ የማእከላዊ መርማሪዎችም ሆነ የማረሚያ ቤት ኃላፊዎች ውስጥ እስካሁን በህግ ተጠያቂ የሆነ አለመኖሩ እንዳሳዘናቸው ጉዳተኞች ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment