Monday, July 30, 2018

በአማሮ ወረዳ እና በጉጂ መካከል እንደገና ግጭት በማገርሸቱ የሰዎች ሕይወት አለፈ

(ኢሳት ዜና ሃምሌ 23 ቀን 2010 ዓ/ም ) በድንበር በማካለል ስም የተነሳውና ለአንድ አመት ያክል የዘለቀው በአማሮ ወረዳ በሚኖሩ የኮሬ ብሄረሰብና በጉጂ ኦሮሞ መካከል የተከሰተው ግጭት ዛሬ ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፣ ዛሬ ከዲላ ወደ አማሮ ኤፍ.ኤስ.አር የጭነት መኪና ሲያሽከረክር የነበረ፣ በጀሎ ቀበሌ ቅዱስ ዮሃንስ ቤተ-ክርስቲያን ፊት ለፊት የታጠቁ ሃይሎች ተኩስ በመክፈት ሹፈሩን ጨምሮ ሌላ አንድ ተሳፋሪ ወዲያዉ በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል። ይህንን ተከትሎም ተኩስ በሁለቱ ወገን ተከፍቶ በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ የተኩስ ልዉወጥ እየተደረገ እንዳለና እስከ አሁን ሰዓት በኮሬ በኩል ብሻሮ ዘለቀ የሚባል አርሶአደር እንደተገደለ፣ ሌሎች ሶስት ደግሞ ቆስለዉ ኬሌ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸዉ እንደሆነ የደረሰን መረጃ ያመለክታል። በአካባቢዉ የመከላከያ አባላት ቢኖሩም፣ ግጭቱን ማስቆም እንዳልቻሉ በተለይ መከላከል ያልቻሉት ደግሞ
መኖሪያቸዉ ከተማ ላይ ስለሆነ ከግጭት ከአካባቢዉ 20 ኪሜ ርቀት ላይ እንደሚኖሩ በህብረተሰቡም ቅሬታ እየፈጠረ እንዳለ ግጭቱ ላይ ዘግይቶ በአካባቢዉ ከደረሱት መከላከያዎች መሃልም አንዱ በጥይት ተመትቶ እንደቆሰለ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል። ከቡሌ ሆራና ከወረዳዉ ቆላማ ቀበሌዎች በተለይ ከዶርባዴና ጀሎ፣ የተፈናቀሉ ከ 21 ሺ 800 በላይ ዜጎችም ጉዳይ በኢሳት በተደጋጋሚ መዘገቡን ተከትሎ፣ የሃገር ዉስጥ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ለመስጠት ቢሞክሩም፣ አስከ ዛሬ በቂ እገዛ በማጣት ለከፋ ችግር ተጋልጠው ይገኛሉ። ከሃምሌ 16 ቀን 2009 ዓም ጀምሮ የሞቱት ዜጎች ቁጥር ከአማሮ ብቻ 60 የቆሰሉት ደግሞ 114 መድረሱን መረጃዎች ያመለክታሉ።

No comments:

Post a Comment