Thursday, March 10, 2016

አጣዳፊ ተቅማትና ትውከት በደቡብ፣ ሶማሊያና ኦሮሚያ ክልሎች እየተዛመተ ነው ተባለ

ኢሳት (የካቲት 30 ፥2008)

ከቀናት በፊት በደቡብ ክልል አርባ ምንጭ ከተማና ዙሪያዋ ባሉ አካባቢዎች የተከሰተው የአጣዳፊ ተቅማትና ትውከት (አተት) በሽታ በሶማሊያና ኦሮሚያ ክልሎች በመዛመት ላይ መሆኑን የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ረቡዕ አስታወቀ።
በዚሁ በሽታ እየተያዙ ወደህክምና ጣቢያዎች የሚሄዱ ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን የህክምና ባለሙያዎች ገልጸዋል።

የንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት እጥረትና የንጽህና መጓደል በሽታውን በወረርሽኝ መልክ እንዲከሰት ማድረጉን የሚናገሩት የህክምና ባለሙያዎች፣ በበሽታው የተያዙ ሰዎች አፋጣኝ የህክምና እርዳታን ካላገኙ የመሞት እድላቸው 50% መሆኑንም አስረድተዋል።
በህብረተሰቡ ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሮ የሚገኘው ይኸው አተት በሽታ በሶማሊ ክልል ሁደት ወረዳ፣ በኦሮሚያ ቦረና ዞን ገላና ወረዳና በደቡብ ክልል አርባምንጭ ከተማ ዙሪያ በመዛመት ላይ መሆኑ ታውቋል።
ከሰው ወደሰው በከፍተኛ ፍጥነት የሚተላለፈውን በሽታ ለመቆጣጠርም የጤና ባለሙያዎችን በማሰማራት ርብርብ እየተደረገ እንደሚገኝ የገለጸው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ህብረተሰቡ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን ወደህክምና ማዕከሎች እንዲወስዱ አሳስቧል።
አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በተለያዩ ክልሎች ተከስቶ ያለው የውሃ እጥረት ለበሽታው አስተዋፅኦ ማድረጉን የህክምና ባለሙያዎች በመግለጽ ላይ መሆናቸውን ከሃገር ቤት የተገኘ መረጃ አመልክቷል።
ይኸው ተላላፊ በሽታ ከአራት አመት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ ተከስቶ በነዋሪዎች ላይ ጉዳት ማድረሱ የሚታወስ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኦሮሚያ ክልል የሞያሌ አካባቢና በሶማሊ የክልል ዞኖች ካለፈው ወር ጀምሮ 149 ሰዎች በበሽታው መያዛቸውን አስታውቋል።
በአርባምንጭ ከተማም ከ40 የሚበልጡ ሰዎች ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኝ የጤና ባለሙያዎች አክለው ገልጸዋል።
ይሁንና፣ የበሽታ ስርጭቱ በሌሎች ክልሎች በመዛመቱ ምክንያት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ተብሎ ተሰግቷል።
የበሽታውን ስርጭት ተከትሎም የአዲስ አበባ የምግብ መድሃኒት የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በመዲናይቱ የጽዳት ቁጥጥር መጀመሩም ታውቋል።

No comments:

Post a Comment