Wednesday, March 23, 2016

ለንግድ ሱቆች በወጣ የሽያጭ ጨረታ አስደንጋ ጭ ዋጋ ተሰጠ።

መጋቢት ፲፬ (አሥራ አራት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በአብዛኛው ባለፈው አመት መጋቢት ወር በ10ኛ ዙር እጣ የወጣባቸው ኮንደሚኒየም ቤቶች ጋር አብረው ለተሰሩ ለንግድ ሱቆች በወጣ ጨረታ አስደንጋጭ ዋጋ ተሰጥቷል።

ንብ ባንክ በልደታ አካባቢ ለሚገኝ የኮንደሚኒየም የንግድ ቤት ለአንድ ካሬሜትር 101 ሺ111 ብር ከ11 ሳንቲም እጅግ የተጋነነ ዋጋ በመስጠት 87 ነጥብ 19 እና 76 ነጥብ 29 ካሬሜትር ሁለት ቤቶችን አሸናፊ ሆኖአል። በአንጻሩ እዚያው ልደታ መልሶ ማልማት አንድ ግለሰብ ለአንድ ካሬሜትር 21 ሺ523 ብር ዋጋ በመስጠት 96 ነጥብ 13 ካሬ ሜትር ቤት አሸናፊ ሆነዋል።
በአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት አነስተኛ በካሬሜትር 15ሺ፣ ከፍተኛው በካሬሜትር 72ሺ ብር ተሸጦዋል። አስተዳደሩ 2 ሺ 398 ያህል የንግድ ቤቶችን ለጨረታ ያቀረበ ሲሆን ለእነዚህ ቤቶች ከ45ሺ በላይ ተጫራቶች ተወዳድረዋል።
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ በመንገድ ላይ አነስተኛ እቃዎችን የሚሸጡ ነጋዴዎች መንግስት የንግድ ቦታዎችን ሳያመቻች በሚወስደው እርምጃ እየተማረርን ነው ብለዋል። የት ሄደን እንነግድ፣ እንዴት እንኑር በማለት ጥያቄ የሚያቀርቡት ነጋዴዎች፣ መንግስት ምቹ ሁኔታ ሳይፈጥር ንብረታችንን መዝረፉ ለከፋ ችግር ዳርጎናል ይላሉ። ፖሊሶች በበኩላቸው ፣ ከላይ የሚሰጣቸውን ትእዛዝ በማክበር የመንገድ ላይ ነጋዴዎችን ንብረት ለመቀማት ሲሄዱ፣ ህዝቡ ተባብሮ ጩኸት በማሰማት ሃላፊነታቸውን እንዳይወጡ እንዳደረጋቸውና የበላይ አለቆቻቸውም ይህን እንዳልተረዱላቸው ይገልጻሉ። በአዲስ አበባ በጎዳና ነጋዴዎችና በፖሊስ መካከል ያለውን ግብግብ የተመለከተ ቪዲዮ በኢሳት ዘጋቢ የተቀረጸ ሲሆን፣ በቪዲዮው ላይ አንድ ነጋዴ ንብረቱን እንዳይቀሙት እያለቀሰ ፖሊሶቹን ሲማጸን ይታያል። ሌሎች ሴቶችም እንዲሁ በለቅሶ ብሶታቸውን ሲገልጹ ይታያል ።

No comments:

Post a Comment