Tuesday, March 22, 2016

የኦህዴድ አባላት አቶ አባይ ጸሃዬ በህግ እንዲጠየቁላቸው ጠየቁ

መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ባለፈው ቅዳሜ በተጠናቀቀው የኦህዴድ የከፍተኛና መካከለኛ አመራሮች ግምገማ ፣ የህወሃቱ መስራችና ነባር ተጋይ አቶ አባይ ጸሃዬ፣ ኦህዴድን በተመለከተ የተናገሩት ንግግር በክልሉ ለደረሰው የሰው ህይወት መጥፋትና ለንብረት ውድመት ዋና ተጠያቂ ነው በማለት ህወሃት አቶ አባይን ገምግማ ለፍርድ እንድታቀርብ ጠይቀዋል።


ቤቱ በውይይቱ ” ችግራችን የመስመር ወይም የአላማ ችግር ሳይሆን የአመራር ችግር ነው” የሚል ውሳኔ ቢያስተላልፍም ፣ ይህን ችግር ለመፍታት ከህዝብ ጋር በመገምገምና በአጥፊዎች ላይ እርምጃ በመውሰድ የህዝብ ቁጣ ማብረድ ያስፈልጋል የሚል ሃሳብ ከመሪዎች ሲሰነዘር፣ የሃሳብ ልዩነት ተፈጥሯል። አንዳንዶች፣ ችግሩ ከላይኛው አመራር የሚነሳ በመሆኑ በቅድሚያ የላይኛው አመራር ተገምግሞ እርምጃ ይወሰድበት የሚል አቋም አራምደዋል። አንድ አባል “ዛሬ መሬት ሽጣችሁ ስትጨርሱ እኛን አላቅሱን ብላችሁ መጥራታችሁ ትክክል አይደለም፡፡ የሚል አስተያየት የሰጠ ሲሆን፣ እርምጃው ከእናንተ ይጀምር ብሎአል።
ጉባኤውን ከሁለት የከፈለውና ያጨቃጨቀው የአቶ አባይ ጸሃዬ ጉዳይ ሲነሳ እንደነበር ስብሰባውን የተካፈሉ አባላቱ ለኢሳት ዘጋቢ ተናግረዋል።በርካታ የድርጅቱ አባላት፣ በክልላችን ለተፈጠረው ችግር ዋነኛው ተጠያቂ አቶ አባይ ጸሃዬ ናቸው በማለት አስተያየት የሰጡ ሲሆን፣ አንዳንዶች በስሜት ውስጥ ሆነው “አቶ አባይ ጸሃዬ የኦሮሞ ህዝብ ጠላት ነው፤የኦሮሞን ህዝብ የገደለና ያስገደለ በመሆኑ፣በክልላችን ከእንግዲህ እንዲመጣ እንዳይፈቀድለት፣ በጉልበቱ የሚመጣ ከሆነ ግን የኦህዴድ አባላት አይለቁትም” ብለው የተናገሩ ሲሆን፣ ህወሃት አባይ ጸሃዬ እና ጌታቸው ረዳ በኦሮም ህዝብ ላይ ተገቢ ያልሆነ ነገር ሲናገሩ እርምጃ ባለመውሰዱ ድርጅቱም በኦሮምያ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቄ ነው ብለዋል። አብዛኞቹ ተሳታፊዎች የአቶ አባይ ጸሃዬንና የአቶ ጌታቸው ረዳን ጥፋተኝነት ቢያምኑም፣ መድረኩን የሚመሩት እና ሌሎች ከፍተኛ አመራሮች፣ ህወሃት ተጠያቂ ይሁን የሚለውን አልተቀበሉትም። “ህወሃትና አባይ ጸሃዬን ለይተን እንይ”፣ የሚል ሃሳብ ያቀረቡት ከፍተኛ አመራሮቹ፣ የአቶ አባይንና የአቶ ጌታቸውን ጉዳይ፣ በኢህአዴግ የጋራ ጉዳይ ላይ በማቅረብ አጀንዳ ሆኖ እንዲያዝ ለማድረግ እንደሚሰሩ በመግለጻቸው፣የአቶ አባይ ጸሃዬ ጥፋት በውሳኔው ላይ ሰፍሮ፣ ህወሃት እርምጃ እንዲወስድ የሚጠይቅ የውሳኔ ሃሳብ እንዲሰፈር ሁሉም ተስማምተዋል።
በዚሁ ስብሰባ ላይ የአቶ ዘላላም ጀማነህና የአቶ ዳባ ደበሌም ጉዳይ ተነስቷል። ሁለቱም ሰዎች የቀረበባቸው ክስ ሙስና የሚል ነው። አቶ ዘላለም ከኦህዴድ አባልነታቸው ሙሉ በሙሉ መሰረዛቸው በስብሰባው ላይ ተገልጿል። የምስራቅ ሃረርጌ አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ደምሴ ያቺሳ ፣ ለሰዎች ሹመት ለመስጠት 50 ሺ ብር ጉቦ እንደሚቀበሉና ባለትዳር ሴቶችን ሳይቀር ያባልጋሉ የሚል ክስ የቀረበባቸው ሲሆን፣ እሳቸውም ከሃላፊነታቸው ተነስተው በህግ እንዲጠየቁ ተወስኗል።
የሃረርጌ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት እና አሁን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው የተሾሙት አቶ ረጋሳ ከፍያለው፣ ቀደም ብሎ ሙስና ውስጥ በመግባታቸው ከተገመገሙ በሁዋላ፣ እንደገና መሾማቸው አግባብ ባለመሆኑ፣ ለፍርድ እንዲቀርቡ ተሰብሳቢዎች ጠይቀዋል።
የኦህዴድ የፖለቲካ ክፍል ሃላፊ በመሆን ሲያገልግሉ የነበሩት አቶ ገለሞ፣ በሙስና ተዘፍቀዋል በሚል ተገምግመው ከተባረሩ በሁዋላ፣ አሁንም ፎቅ ሰርተውና በርካታ መኪኖችን ገዝተው እየነገዱ በመሆኑ፣ በህግ ይጠየቁ ሲሉ አባላቱ ጠይቀዋል።
በመጀመሪያው ቀን አባላቱ ስልክና ሌሎችም የድምጽ መቅረጫዎችን ይዘው እንዳይገቡ ጥብቅ ፍተሻ የተደረገባቸው ሲሆን፣ በስብሰባው ማጠቃለያ ቀን ግን ፍተሻው ላልቶ ታይቷል።ይህን በመጠቀም ስልካቸውን ይዘው የገቡ የድርጅቱ አባላት፣ ስብሰባውን ጨርሰው ሲወጡ ፍተሻ የተደረገባቸው ሲሆን፣ በፍተሻው ስልክ የተገኘባቸው አባላቱ ለብቻ እንዲገለሉ ተደርገው፣ ስልካቸው ሲመረመር ውሎአል።
በሌላ ዜና ደግሞ ዛሬ የነቀምቴ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች የተቃውሞ ሰልፍ አድርገው ውለዋል። ተማሪዎቹ አጋዚ ጦር ከአካባቢያቸው እንዲወጣ እንዲሁም የታሰሩት እንዲፈቱ ጠይቀዋል።

No comments:

Post a Comment