Monday, March 28, 2016

በሽብር ወንጀል የተከሰሱት በቀጠሮ ብዛት እየተጉላሉ ነው

መጋቢት ፲፱ (አሥራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ቀደም ብሎ በሽብር ወንጀል የሚከሰሱ የህሊና እስረኞች ጉዳያቸው በከፍተኛው ፍርድ ቤት 19ኛው ችሎት ሲታይ ቢቆይም፣ መዝገቡ በችሎቱ በመከማቸቱ ፣ ካለፉት 9 ወራት ጀምሮ በጸረ ሽብር አዋጁ አንቀጽ 7 የተከሰሱት በ14ኛ ወንጀል ችሎት እንዲቀርቡ ሲደርግ ቆይቷል። የዚህ ችሎት ዋና ዳኛ አቶ አባሆይ ሲሆኑ፣ ዳኛው በተለያዩ ችሎቶች እየተዘዋወሩ ስለሚሰሩ ተከሳሾች ረጃጅም ቀጠሮዎች ይሰጡዋቸዋል። ተከሳሾች በቀተሮዋቸው መሰረት ችሎት ሲገኙ፣ ችሎቱ ዝግ ነው እየተባሉ ችሎት ሳይገቡ ወይም ባሉበት እስር ቤት ረጅም ቀጠሮ እንደተቀጠሩ መልእክት ይደርሳቸዋል።

14ኛ ወንጀል ችሎት ረጅም ቀጠሮ መስጠት ብቻ ሳይሆን ረጅም የእስር ውሳኔ በመስጠትም ይታወቃል፡፡ የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴዎችን ለመተካት ስትሰሩ ነበር ተብለው የተከሰሱት እነ ኤልያስ ከድር 7 አመት የተፈረደባቸው በዚህ ችሎት ነው።
ከአርበኞች ግንቦት7ት ጋር በተያያዘ የተከሰሱት እነ አቶ ብርሃኑ ተክለያሬድ ፣ በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን መዝገብ የተከሰሱ 16 ሰዎች፣ በእነ ከድር ሙሃመድ የተከሰሱ 20 ሰዎች፣ በእነ ማስረሻ ታፈረ ወልደገብርኤል መዝገብ የተከሰሱ 10 ሰዎች እንዲሁም በመቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠብሬ መዝገብ የተከሰሱ 6 ሰዎች ያለቀጠሮ በእስር ቤት እየተሰቃዩ የሚገኙት በ14ኛው ችሎት በሚሰጥ ውሳኔ ነው።
በእነ መቶ አለቃ ጌታቸው መኮንን፣ እነ ማስረሻ ታፈረ ወልደገብረኤልና መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጠብሬ መዝገብ የተከሰሱ 32 ተከሳሾች ክሳቸው ተቋርጦም ከሆነ እንዲነገራቸው ካልሆነም ደግሞ እንደማንኛውም እስረኛ የቀጠሮ ቀናቸውን አውቀው ክሳቸውን እንዲከታተሉ ለፍትህ ሚኒስቴር ድብዳቤ ጽፈው የእስር ቤቱ አስተዳደር ማህተም አድርጎ እንዲሰጣቸው ማመልከቻ ቢያስገቡም ደብዳቤው ተመልሶ እንዳልተሳጣቸው እስረኞች ለኢሳት በላኩት መረጃ ላይ ገልጸዋል።

No comments:

Post a Comment