Tuesday, March 22, 2016

በአዲስ አበባ ከተማ የውሃ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል

መጋቢት ፲፫ (አሥራ ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነዋሪዎች እንደሚሉት በተለይ በአራት ኪሎ ቤተ መንግስት አካባቢ፣ መገናኛ፣ ልደታ፣ ኮተቤ፣ ጉርድ ሾላ፣ አብነት አካባቢ ችግሩ በከፋ ሁኔታ ተባብሶ ቀጥሏል።

የአካባቢው ነዋሪዎች ለአራት ቀናት ያክል ውሃ ማግኘት እንዳልቻሉና በዚህም ሳቢያ እናቶች ልጆቻቸውን ምግብ አብስሎ ለመመገብና ንጽሕናቸውን ለመጠበቅ እንዳልቻሉ ነዋሪዎቹ አስታውቀዋል።

አቅሙ ያላቸው የታሸገ ውሃ በመግዛት ሲጠቀሙ ድሃው አብዛሃኛው የከተማዋ ነዋሪ ግን የቧንቧ ውሃን በተስፋ ከመጠበቅ ሌላ በከተማዋ መስተዳድር በኩል የቀረበለት አማራጭ አለመኖሩ የእለት ተእለት እንቅስቃሴያቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ አሳድሯል።
በሆቴልና አገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ የከተማዋ ነጋዴዎችም ደንበኞቻቸውን ማስተናገድ የተሳናቸው ሲሆን፣ በሕክምና ተቋማትና በመማር ማስተማሩ ላይም የውሃ ችግሩ ከፍተኛ ችግር መኖሩ እየተነገረ ነው።
ከሳምንታት በፊት ከእኩለ ለሊት በኋላ ጭል ጭል እያለ ይመጣ የነበረው ውሃ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ በመቋረጡ ለችግር መዳረጋቸውን በአጽኖት አስረድተዋል። ለችግራቸው አፋጣኝ እልባት የሚሰጣቸው አካል ማጣታቸውንና መወትወታቸውን እንዳላቋረጡ ምንጮች በተለይ ለኢሳት ተናግረዋል።

No comments:

Post a Comment