Tuesday, March 15, 2016

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ

ኢሳት (መጋቢት 6 ፥ 2008)

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ኦሮሚያ ክልል እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ዙሪያ እርምጃዎችን እንዲወስድ ሂውማን ራይትስ ዎች ማክሰኞ ጥያቄውን አቅርቧል።
ምክር ቤቱ በክልሉ እየተፈጸመ ባለው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ዙሪያ ስጋቱን ይፋ እንዲያደርግ የጠየቀው ሂውማን ራይትስ ዎች ምክር ቤቱ የኢትዮጵያ መንግስት ከሚወስደው የሃይል እርምጃ እንዲቆጠብ ግፊትን እንዲያደርግ አሳስቧል።
ተቃውሞውን ተከትሎ ለእሰር የተዳረጉ ሰዎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ለኢትዮጵያ መንግስት ጥያቄውን ማቅረብ እንዳለበትም የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቱ ባቀረበው ጥያቄ አመልክቷል።
የተለያዩ አካላትን ያካተተ ገለልተኛ የአጣሪ ቡድን ተቋቁሞ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙ ግድያዎችንና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር እንዳለበትም ሂውማን ራይትስ ዎች አክሎ ጠይቋል።
በኢትዮጵያ በስድስት ክልሎች ተከስቶ ያለው የድርቅ አደጋ ረሃብን ያስከትላል የሚል ስጋት ማሳደሩንና ችግሩ በቂ አለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ስፋን አለማግኘቱ እንዳሳሰበው የአለም አቀፉ የካቶሊክ ጥምረት አስታወቀ።
በወቅታዊ የኢትዮጵያ የድርቅ ዙሪያ ሪፖርትን ያቀረበው ይኸው የእርዳታ ተቋም የድርቁ አደጋ እየተባባሰ በመሄድ ላይ ቢሆንም በቂ የመገናኛ ብዙሃን ሽፋን ሊያገኝ አለመቻሉን ገልጿል።
በአፋርና በትግራይ ክልሎች ድርቁ እያደረሰ ያለው ጉዳት ከሚነገረው በላይ መሆኑን በሪፖርቱ ያሰፈረ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ አለም አቀፍ ድጋፍ በወቅቱ ወደ ሃገሪቱ ሊደርስ አለመቻልን ችግሩን እያባባሰው እንደሆነ አመልክቷል።
የአለም አቀፍ የኦርቶዶክስ ክርስቲያን የበጎ አድራጎት ተቋም በበኩላቸው ድርቁ ባደረሰው ጉዳት ከ400ሺ የሚበልጡ እንስሶች ማለቃቸውን እና ችግሩ የከፋ እየሆነ መምጣቱን ገልጿል።
በኢትዮጵያ የካቶሊክ የእርዳታ አገልግሎት ተወካይ የሆኑት ማትዲቪስ በበኩላቸው ድርቁ በርካታ ህዝብ በሚኖርበትና ሰፋፊ የእርሻ ቦታዎች በሚገኙባቸው አካባቢዎች በመከሰቱ ምክንያት ችግሩ አሳሳቢ ሊሆን መቻሉን አሌቲያ ለተሰኘና በሰብዓዊ እርዳታዎች ዙሪያ ለሚሰራ መጽሄት አስረድተዋል።
በሃገሪቱ ያለው የድርቅ አደጋ የ1977ቱን አይነት ረሃብ ባይሆንም ተመሳሳይ ይዘትን እያሳየ እንደሚገኝ የካቶሊክ እርዳታ አገልግሎት ተወካይ የሆኑት ማት ዴቪስ አክለው ገልጸዋል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ሌሎች አለም አቀፍ የእርዳታ ተቋማት ድርቁ ወደ ረሃብ ሊለወጥ ይችላል የሚል ስጋትን በማሰማት ላይ ቢሆኑም የመንግስት ባለስልጣናት ድርጅቶቹ ችግሩን አጋነውታል በማለት ማስተባበያን ሰጥተዋል።
ይሁንና ከ10 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ተረጂዎች ያለው የምግብ አቅርቦት በቀጣዩ ወር የሚያልቅ በመሆኑ የድርቁ ጉዳት ወደከፋ ደረጃ ሊሸጋግር እንደሚችል እነዚሁ ተቋማት አሳስበዋል።
የአለም ምግብ ፕሮግራም በድርቁ ሳቢያ እየደረሰ ያለው ጉዳት በመባባሱም ረሃብ እንዲከስት ያደርጋል የሚል ስጋት ማሳደሩን የተለያዩ አካላት በመግለጽ ላይ ናቸው።

No comments:

Post a Comment