Tuesday, March 8, 2016

የአማራ ክልል የምክር ቤት አባላት በርካታ ጥያቄዎቸን አቀረቡ

የካቲት ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ክልሉ በሚያደርገው 5ኛ ዙር 3ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ ከተለያዩ ዞኖች የተወከሉ የምክር ቤት አባላት በመቶዎች የሚቆጠሩ ጥያቄዎችን ጽፈው ለውይይት አቅርበዋል።

ጥያቄዎቹ፣ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊ፣ ጸጥታና አስተዳዳር የተመለከቱ ናቸው።
የምክር ቤት አባላቱ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የውሃ እጥረት መፈጠሩንና ችግሩ አለመቀረፉን፣ በእርዳታ የሚሰጠው በቆሎ በቂ አለመሆን፣የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተማሪዎች በድርቅ ምክንያት ቤተሰቦቻቸውን መርዳት ባለመቻላቸው ትምህርታቸውን ማቋረጣቸው፣ በድርቅ በተጎዱ አካባቢዎች በሚገኙ ከተሞች የምግብ አገልግሎት እደላ አለመጀመር ፣ አገልግሎት ዘመኑ ያለፈበት ማዳበሪያ እየታደለ መሆኑ፣ እርዳታ የሚፈልጉና እርዳታ የሚሰጣቸው ቁጥር አለመመጣጠን ፣
መንግስት ለወር ከሚሰጠው 15 ኪሎ ግራም እርዳታ ጋር ዘይትና ክክ አብሮ ይሰጣል ተብሎ ቢነገርም፣ እየተሰጠ አለመሆኑ፣ በምእራብ በለሳ፣ ዝቋላ፣ ሰሃላ፣ ዋግ ህምራ ዜጎች በድርቅ የተነሳ መሰደዳቸው፣ ተሰደው ባህርዳርና ጎንደር ለገቡት ስለሚደረገው ድጋፍ ጥያቄዎች ቀርበዋል።
በክልሉ ከፍተና የሆነ የመምህራን ፍልሰት መኖሩ፣ በተለይም በሰሜን ሸዋ ችግሩ መስፋቱ ተነስቷል።
ጸጥታን በተመለከተ ከተነሱት ጥያቄዎች መካከል ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ፣ ከትግራይ ክልል ጋር ያለው የድንበርና የማንነት ጥያቄ እንዲሁም የሱዳን ድንበር ጥያቄ ዘላቂ መፍትሄ ለምን ሊሰጥ እንዳልቻለ፣ በክልሉ የወረዳ ይከፈልልኝ ጥያቄ እየበዛ መመጣቱ፣ በተለያዩ የአገሪቱ ክልሎች የሚማሩ በተለይ በአማራ ተወላጆች ላይ በደል እየደረሰባቸው በመሆኑ ክልሉ ስለሚወስደው እርምጃ፣ የአማራ ክልል ተወላጆች ሌሎች ክልሎች ሄደው በነጻነት ለመስራት ባለመቻላቸው ከፍተኛ ችግር እያጋጠማቸው መሆኑ፣ ቤታቸው እየተቃጠለ ንብረታቸውም እየተዘረፈ እያለ ክልሉ ግምገማ ማድረግና አለማድረጉ በጥያቄ መልክ ቀርቧል።
የብሄር ግጭቶች እየተባባሱ፣ ከአጎራባች ወረዳዎች ጋር መኖር አስጊ ደረጃ ላይ የተደረሰ ቢሆንም፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት በሪፖርታቸው ቀለል አድርገው ማቅረባቸው ትክክል አለመሆኑ፣ የጸጥታ ሃይሎች በየአካባቢው ወንጀሎችን እየፈጸሙ መሆኑ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ወረቀቶች እየተበተኑ መሆኑ፣ቅስቀሳዎች እየተደረጉ መሆኑ፣ በክልሉ የፖሊስ አባላት እጥረትና ፍልሰት ከፍተኛ መሆኑ፣ በተለይ በሰሜን ሸዋ አካባቢ ፖሊስ ሌላቸው ቀበሌዎች መኖራቸው በምክር ቤት አባላት ተነስቷል።
ህገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርና ሽያጭ እየተስፋፋ መምጣቱ፣ በተለይ በጎንደር የመሳሪያ ንግዱ ከፍተኛ መሆኑም ተመልክቷል። ከመልካም አስተዳደር ጋር በተያያዘ እርምጃ እተወሰደ ያለው በቀበሌ አመራሩ ላይ እንጅ በከፍተኛ አመራሩ ላይ አይደለም የሚል ቅሬታም ተነስቷል።
የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ባቀረቡት ሪፖርት፣ 21 በመቶ የሚሆነው የክልሉ ህዝብ በእርዳታ እየኖረ መሆኑን ገልጸዋል።
ከቅማንት ጋር በተያያዘ በተነሳው ግጭት በርካታ ሰዎች መሞታቸውን ቢገልጹም፣ የሟቾቹን ቁጥር ሳይገልጹ አልፈውታል።

No comments:

Post a Comment