Monday, March 14, 2016

በኮንሶ ሁለት ሰዎች ተገደሉ


መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- የማንነትና የአስተዳደር መካለል ጥያቄዎች መዘጋታቸውን ጠ/ሚኒስትር ሃይለማርያም ደሳለኝ ባወጁ ማግስት በኮንሶ 2 ሰዎች ተገድለዋል።
እሁድ መጋቢት 4፣ 2008 ዓም የደቡብ ክልል ልዩ ሃይል ወደ ደበና ቀበሌ በመግባት ኤፍትስ በምትባል መንደር ላይ በአርሶአደሮች ላይ ተኩስ ከፍተው፣ ፋንታዬ ኮሪያ ኮንቴ እና ዳንኤል ቱሉ ከሮ የተባሉ ጎልማሶችን መግደላቸውን ሌሎችን ወጣቶችም ማቁሰላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ለኢሳት ተናግረዋል። ነዋሪዎቹ እንዳሉት በፖሊስ ኮሚሽነሩ ፍስሃ ጋረደው የሚመራው ልዩ ሃይሉ ጥቃቱን የፈጸመው፣ ምንም አይነት እንቅስቃሴ ባልታዬበት ሁኔታ ነበር። የልዩ ሃይል አባላቱ የሟቾቹን አስከሬን ለመደበቅ ጥረት ሲያደርጉ ህዝቡ ደርሶ ማስጣሉን ነዋሪዎች ገልጸዋል።
አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ከእንግዲህ የአስተዳደር ማካለል ጥያቄ ተቀባይነት የለውም በማለት የተናገሩት፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች ያስቆጣ ሲሆን፣ ነዋሪዎቹ ጥያቄያቸው እስከሚመለስ ድረስ ትግላቸውን እንደሚገፉበት አስታውቀዋል።
እስከዛሬ በዘለቀው ተቃውሞ ከ200 ያላነሱ ሰዎች ታስረዋል። ትምህርት ቤቶችና የመንግስት መስሪያ ቤቶችም እንደተዘጉ ናቸው።

No comments:

Post a Comment