Friday, March 25, 2016

በኢትዮጵያ የተከሰተው ረሀብ እጅግ አስፈሪ ደረጃ ላይ መድረሱን የዓይን ምስክሮች በተለይ ለኢሳት ገለጹ።

መጋቢት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርቁ በተለየ መልኩ በከፋባቸው እንደ ሶማሌና አፋር ባሉ ክልሎች ሁኔታውን ተዘዋውረው የተመለከቱ የረድኤት ሰራተኞች ለኢሳት እንደተናገሩት ፤ በተጠቀሱት ክልሎች ባሉ የማገገሚያ ጣቢያዎች ከመክሳታቸው ብዛት ቆዳቸው አጥንታቸው ጋር የተጣበቀና ጭንቅላቶቻቸው ብቻ የቀሩ ህጻናት በሞት ቋፍ ላይ ሆነው እያጣጣሩ ይታያሉ።


በህይወቴ በረሀብ ሳቢያ የዚህ አይነት ዘግናኝ ነገር ሲከሰት ዓይቼ አላውቅም የሚሉት አቶ መስፍን የተባሉ የረድኤት ሰራተኛ፤ የህጻናቱን ሁኔታ ሲመለከቱ አምርረው ማልቀሳቸውን አልሸሸጉም።
በተለይ በጂጂጋ ዙሪያ፣ በሺንሌ እና በተለያዩ የሶማሌ ክልል ዞኖች ድርቁና ረሀቡ እጅግ አስከፊ ደረጃ ላይ በመድረሱ የሚጠጡት ውሀና የሚበሉት ግጦሽ ያጡ እንሥሳት በየቦታው ወድቀው እንደሚታዩ የረዴት ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች አንድ ኪሎ ስጋ እስከ 200 ብር በሚሸጥበት በአሁኑ ወቅት በድርቅና በረሀብ በተጎዱ አካባቢዎች ያሉት በርካታ አርብቶ አደሮች እንሥሶቻቸው ከመሞታቸው በፊት ወደ ከተሞች በመምጣት በወደቀ ዋጋ መሸጥ መጀመራቸውን የዓይን እማኞቹ ገልጸዋል።
በሶማሌ ክልል በአፍዴምና በሙሉ ጤና ጣቢያዎች በረሀብ ሳቢያ የሞት ጣር የሚያቃስቱ ህጻናት እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታ እንደሚታዩ የጠቀሱት አቶ መስፍን፤ “ሁኔታው ራስህን እንድትጠላ የሚያደርግ ነው” ይላሉ።
መንግስት ለገጽታ ግንባታ በሚል ስላለው ሁኔታ መረጃ እንዳይወጣ በጥብቅ እየተከላከለ መሆኑን የጠቀሱት የረድኤት ሰራተኛው፤ እንደምንም ብለው በድብቅ ያነሱትን የአንድ የአራት ዓመት ህጻን ፎቶግራፍ ለኢሳት ልከዋል።
ይህ በምስሉ ላይ የሚታየው በረሀብ የተጎዳ የአራት ዓመቱ ህጻን ፎቶግራፍ የተወሰደው ከሶማሌ ክልል ከሙሉ ጤና ጣቢያ መኾኑንም የረዴት ሰራተኛው ተናግረዋል።
ሰዎች እንደ ቅጠል እየረገፉ ባለበት ወቅት መንግስት “ገጽታ ግንባታ” ለሚለው ነገር ይበልጥ በመጨነቁ፤ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተሯሩጠው በሞት አፋፍ ላይ ላሉት እንዳይደርሱና ድጋፍ እንዳያደርጉ እንቅፋት መፍጠሩን የእርዳታ ሰራተኞቹ ይናገራሉ።
ይሁንና መንግስት መረጃው እንዳይወጣ ምንም በጥብቅ አፍኖት ቢገኝም፤ የረድ ኤት ሰራተኞች ተጨማሪ ፊቶግራፎችንና ቪዲዮዎችን እንደምንም ብለው በመቅረጽ በኢሳት በኩል ሁኔታውን ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ለማጋለጥ ጥረት እንደሚያደርጉም ቃል ገብተዋል።
የአይን ምስክሮቹ ከሶማሌ ክልል በተጨማሪ በአፋር ክልል በስደተኞች ካምፕ ውስጥ በረሀብ ሳቢያ አጥንታቸው የሚቆጠሩ ህጻናት እጅግ በሚዘገንን ሁኔታ እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ “ በካምፑ ውስጥ ያዩት ትእይንት መቼም ቢሆን ከአእምሯቸው እንደማይጠፋ ተናግረዋል።
ኔዘርላንድ 2 የተሰኘው የቴሌቪዥን ቻነል የኢትዮጵያን ረሀብ አስመልክቶ ከትናንት በስቲያ ባስተላለፈው ዘጋቢ ፊልም፤ በተለይ በአፋር ክልል በረሀብ ምክንያት ክፉኛ የተጎዱ ህጻናትን አሳይቷል። ህጻናቱ በቂ ምግብ ባለማግኘታቸው ክፉኛ መጎዳታቸውን አንድ የእርዳታ ሰራተኛ ዘጋቢ ፊልሙን ለሰራው ጋዜጠኛ ለቫን ዶንገን ነግሮታል።
እስከ አምስት እና ስድስት አባላት ላሉት አንድ ቤተሰብ በየአራት ቀኑ 20 ሊትር ውሀ እየታደለ መኾኑን የጠቀሰው የረድኤት ሰራተኛው፤ 20 ሊትሩ ውሀ የሚሰጠው ለመጠጥ ባቻ ሳይሆን ለሁሉም ዓይነት አገልግሎት እየተባለ እንደሆነ ተናግሯል።
በድርቁ ምክንያት የለገዳዲ ግድብ ባለመሙላቱ ነው በሚል የአፍሪካ መዲና በሆነችው በአዲስ አበባ ሳይቀር በቅርቡ የውሀ አገልግሎት በፈረቃ መጀመሩ ይታወቃል።
ረሀቡ የደረሰበትን አስከፊና ዘግናኝ ሁኔታ በ ዓይናቸው እያዩ ባለበት ሁኔታ ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት “ለገጽታ ግንባታ” በሚል አደባባይ እየወጡ “የምግብ ዋስትና አረጋግጠናል፤ በምግብ ሰብል ራሳችንን ችለናል” እያሉ የሚሰጡት መግለጫ እጅግ እንደሚያሳዝናቸውና እንደሚያበሳጫቸው እነኚሁ የኢሳት ምንጮች ገልጸዋል። የጠቅላይ ሚኒስትሩ አማካሪ ዶክተር አርከበ እቁባይ በቅርቡ ከብሉምበርግ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ፦” በምግብ ሰብል ራሳችንን ችለናል፤ የምግብ ዋስትና አረጋግጠናል” ማለታቸው ይታወሳል።
ዶክተር አርከበ ይህን ቢሉም በማግስቱ አቶ ኃይለማፘም ደሳለኝ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ የድረሱልን ጥሪ ማቅረባቸውም ይታወቃል። ዘንድሮ በኢትዮጵያ 18 ሚሊዮን ሕዝብ አስቸኳይ የምግብ እርዳታ እንደሚፈልግ ዓለማቀፍ መገናኛ ብዙሀን እየዘገቡ ነው።
አንዳንድ ዓለማቀፍ የእርዳታ ድርጅቶች የተረጅውን ቁጥር 20 ሚሊዮን ያደርሱታል። ሀገሪቱ ጫፍ እስከ ጫፍ በህዝባዊ ተቃውሞ እየተናጠች ባለበት በዚህ ወቅት ረሀብ የከፋ በትሩን ማሳረፉ፤ የሚከሰተውን እልቂት ከማባባሱም በላይ ለስርዓቱ ህልውና አደገኛ እንደሚሆን ታዛቢዎች ስጋታቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
እንደ ዩናይትድስቴትስ ያሉ የስር ዓቱ ደጋፊዎች በሀገሪቱ የዓለማቀፍ የልማትና የ እርዳት ኤጀንሲ ኃላፊ በጋይለ ስሚዝ አማካይነት በግልጽ “ ወዳጃችንን ለማዳን”በሚል በቅርቡ ከ532 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት እርዳታ ቢሰጡም ፤ በሀገሪቱ ከተከሰተው የድርቅ መጠን ስፋት አኳያ ድጋፉ ኢምንት ነው።
በመሆኑም ሁኔታው የከፋ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከትላል ብለው የሰጉ አንዳንድ ም እራባውያን ሀገራትም የእርዳታ ቁሳቁሶችን መላክ ጀምረዋል። 20 ሚሊዮን ያህል ህዝብ ለረሀብና ለአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ ሲዳረግ በኢትዮጵያ ታሪክ የአሁኑ የመጀመሪያ ነው።
በኢትዮጵያ የረሀብ ጉዳይ በተለይ በአጼ ኃይለስላሴና በወታደራዊው ደርግ አገዛዞች ህልውና ላይ ያሳረፈው ተጽ እኖ ጉልህ እንደነበር የታሪክ ድርሳናት ይናገራሉ።
ከ50 በኋላ በተከሰተ አስከፊ ድርቅ ሳቢያ የተከሰተ ነው የተባለው የአሁኑስ ርሀብ ሁኔታ ወዴት ያመራ ይሆን ? የሚለውን ወደፊት የምናየው ይሆናል።

No comments:

Post a Comment