Friday, March 4, 2016

አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በምስክርነት ለማቅረብ የተደረገው ጥረት ውድቅ ተደረገ

የካቲት ፳፭ (ሃያ አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ነገረ ኢትዮጵያ እንደዘገበው በእነ ዘላለም ወርቃገኘሁ የክስ መዝገብ በአንደኛ ተከሳሽ አቶ ዘላለም ወርቃገኘሁ ላይ በቀረበው ክስ፣ ተከሳሹ ከግንቦት ሰባት ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ ጋር መጻጻፉን አቃቢ ህግ በክሱ ውስጥ ማስፈሩን ተከትሎ፣ ተከሳሽ አቶ አንዳርጋቸው ለምስክርነት እንዲጠሩላቸው ሲወተውቱ ቆይተዋል።ይሁን እንጅ እስር ቤቱ አቶ አንዳርጋቸውን ማቅረብ ባለመቻሉ፣ተከሳሽ ከአቶ አንዳርጋቸው ጋር በተያያዘ የቀረበባቸው ክስ እንዲሰረዝላቸው ጠይቀዋል። አቃቢ ህግ በበኩሉ ተከሳሹ ምስክሩን አቅርቦ የማሰማት ግዴታ እንዳለበት በመጥቀስ ተከሳሹ የጠየቀው የፍሬ ነገር ይውጣልኝ አቤቱታ የህግ አግባብነት የተከተለ ስላልሆነ ምስክሩን እንደተዋቸው ተቆጥሮ ብይን እንዲሰጠው ጠይቋል። ችሎቱም በተከሳሽ የቀረበው አቤቱታ ተቀባይነት እንደሌለው በማስረዳት ምስክሩ እንደተተወ ይቆጠራል ሲል በአቃቢ ህግ የቀረበውን መከራከሪያ ተቀብሎ ውሳኔ ሰጥቷል።

ፍርድ ቤቱ በመዝገቡ ላይ በተካተቱት አምስት ተከሳሾች ላይ የፍርድ ብይን ለመስጠት ለመጋቢት 29/2008 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

No comments:

Post a Comment