Friday, March 25, 2016

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ስልጣናቸውን ለቀቁ።

መጋቢት ፲፮ (አሥራ ስድስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በገዛ ፍዳቸው ስልጣናቸውን የለቀቁት አቶ ሀብቴ ፊቻላ በሁለት ወራት ልዩነት ውስጥ የፌዴራል ፍ/ቤቶችን ከለቀቁ ከፍተኛ ባለስልጣናት መካከል አራተኛው ሆነዋል።

ባለፈው የካቲት ወር የመጀመሪያ ሳምንት የጤና እክል ገጥሞኛል በሚል በገዛ ፈቃዳቸው ከሀላፊነታቸው የለቀቁት የፌዴራል ጠ/ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት እና የህገመንግስት አጣሪ ጉባኤ ቁልፍ ሰው የነበሩት አቶ ተገኔ ጌታነህ ነበሩ።
አቶ ተገኔን ተከትሎ የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ውብሸት ሽፈራው እንዲሁም የፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት ፕሬዚደንት የነበሩት አቶ ደሳለኝ በርሄ ስራቸውን ለቀዋል።

አፈጉባኤ አቶ አባዱላ ገመዳ አቶ ሀብቴ ፊቻላ ከመጋቢት 15 ቀን 2003 ዓም ጀምሮ በሀላፊነት ሲያገለግሉ ቆይተው በገዛ ፈቃዳቸው ስራ ለመልቀቅ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት፣ ከየካቲት 1 ቀን 2008 ዓም ጀምሮ እንዲሰናበቱ የዳኞች አስተዳደር ጉባኤ መወሰኑን ለፓርላማ አባላት አሳውቀዋል። አባ ዱላ ም/ፕሬዚደንቱ የለቀቁበትን ምክንያት ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
የአስፈጻሚ አካላት በቀጥታና በተዘዋዋሪ መንገዶች በፍ/ቤቶች ስራ ውስጥ ጣልቃ መግባቱ እየተጠናከረ መምጣቱ ከፍተኛ የኢህዴግ ደጋፊ ናቸው የሚባሉ ዳኞችንና የፍ/ቤት መሪዎችን ሳይቀር ከስራቸው ራሳቸውን እንዲያገሉ ትልቅ ምክንያት ሳይሆን እንደማይቀር ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

No comments:

Post a Comment