Monday, March 7, 2016

አህዴድ አቶ ዘላለም ጀማነህን አባረረ

የካቲት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በኦሮምያ ክልል የተነሳው ተቃውሞ በተለያዩ አካባቢዎች በመካሄድ ላይ ባለበት በዚህ ወቅት፣ ኦህዴድ ነባር አመራሮቹን ከሃላፊነት ማንሳቱን ቀጥሎአል። ቀድም ብለው ያለማእከላዊ ኮሚቴው እውቅና በስራ አስፈጻሚው ትእዛዝ ብቻ ተባረው ከነበሩት መካከል የአቶ ዳባ ደበሌ መባረር በማእከላዊ ኮሚቴው ሲጸድቅ፣ ” ከዚህ በሁዋላ ከኢህአዴግ ጋር አብሬ አልሰራም” ብለዋል ተብሎ ሲነገርላቸው የሰነበተው የኢህዴድ እና የኢህአዴግ የስራ አስፈጻሚ አባል እና የክልሉ የእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሃላፊ አቶ ዘላለም ጀማነህ ከማንኛውም የድርጅቱ እንቅስቃሴ ታግደዋል።

በአዳማ በመካሄድ ላይ ባለው የኦህዴድ አባላት ግምገማ ባለፉት ወራት ህዝባዊ አመጹን ለማክሸፍ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል የተባሉ የመከላከያ፣የፌደራል ፖሊስ፣የክልሉ ፖሊስ፣ሚሊሽያና የጸጥታ ዘርፍ ከፍተኛ አዛዦች፣ በተለይ በክልሉ የቆዩና አሁንም ያሉ በየደረጃው የሚገኙ የመከላከያ ዋና ዋና አዛዦች ተሳታፊ ሆነዋል። መድረኩ በልዩ ጥንቃቄ እየተመራ አመጽን ሙሉ በሙሉ ሊያከሽፉ የሚችሉ ዘርፈ ብዙ ስትራቴጅዎችን ሊያስተጓጉሉ ይችላሉ የተባሉ አመራሮች በግምገማ የሚመቱበት ጥልቅ ግምገማ በመካሄድ ላይ ነው።
በሌላ በኩል የቀድሞው የክልሉ የጸጥታ ዘርፍ ሃላፊ አቶ ሰለሞን ከቹ ከክልሉ ጸጥታና አስተዳደር ዘርፍ ተነስቶ የፕሬዚደንቱ አማካሪ ሆኖ መሾሙን ምንቾች ገልጸዋል። አቶ ሰለሞን በደህንነት ስራው ብዙ ሚስጢሮችን ስለሚያውቅ ከኢህአዴግ ላለማራቅ ተብሎ የተወሰደ እርምጃ ሳይሆን እንደማይቀር ምንጮች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።
እሱን የተካውና የጠ/ሚኒስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ እንዲሁም የኦህዴድ/ ኢህአዴግ ስራ አስፈጳሚ አባል አቶ በዙ ዋቅቤካ ነው። አቶ ሰለሞን በመልካም አስተዳደር ችግርን በማባባስ፣ በኦሮሚያ የተከሰተውን አመጵ መቆጣጠር ባለመቻል ተገምግሞ
ከቁልፍ ቦታው ከተሰናበተ በሀላ በአማካሪነት መመደቡ ብዙዎችን አስገርሞአል።

No comments:

Post a Comment