Monday, March 14, 2016

ሰመጉ በኦሮምያ የተገደሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር በፎቶ አስደግፎ አወጣ


መጋቢት ፭ (አምስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- በመንግስት ጫና የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ የሚለውን ስሙን ወደ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ እንዲቀይር የተገደደው ሰመጉ፣ ያለበትን ጫና ተቋቁሞ ከህዳር 2 እስከ የካቲት 12፣ 2008 ዓም በኦሮምያ ክልል በ9 ዞኖች ፣ በ33 ወረዳዎች በመንግስት የጸጥታ ሃይሎች የተገደሉትን ሰዎች ስም ዝርዝር ይዞ ወጥቷል። ድርጅቱ በመግለጫው፣ ተቃውሞው እስካሁን የቀጠለ ፣ በአብዛኛው የኦሮሞያ ወረዳዎች የተካሄደና በመካሄድ ላይ ያለ በመሆኑ፣ የተገደሉ፣ የተጎዱ፣ የታሰሩ ሰዎች ከፍተኛ እንደሚሆን ጠቅሷል። ጉዳት በደረሰባቸው አካባቢዎች ከፍተኛ የሆነ የፖሊስና የሰራዊት ሃይል በየአካባቢው በብዛት በመኖሩ፣ ህዝቡ መረጃ ለመስጠት አመኔታ ማጣቱን ድርጅቴ አክሎ ገልጿል። በአገሪቱ ያለው ፖለቲካዊ ሁኔታ በውጥረት የተሞላ መሆኑ እንደልብ ተዘዋውሮ ለመስራት አለመቻሉንም ገልጿል።
ሰመጉ ከዘረዘራቸው 103 ሟቾች መካከል የግማሽ ያክሉ ፎቶአቸው አብሮ የተያያዘ ሲሆን፣ የሌሎቹ ደግሞ ሙሉ አድራሻቸው ተቀምጧል። በእድሜ እረገድም በአብዛኛው በ20 ዎቹ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ የ12 እና የ13 አመት ታዳጊዎችም ይገኙበታል። በሪፖርቱ እንደተመለከተው በደንዲ ወረዳ ሶምቦላሼቃ ወረዳ በቀለ ሊሌሳ እና ጫልሲሳ ጎንፋ የተባሉ የ20 እና የ18 አመት ወጣቶች ታህሳስ 3 ቀን፣ 2008 ዓም ብርሃኑ ኢፋ በተባለ የአስጎሪ ከተማ የጸጥታ ዘርፍ ጭንቅላታቸውን በጥይት ተመተው ተገድለዋል።
በጀልዱ ወረዳ ደጀኔ ኢብሳ የተባለ የ38 አመት ጎልማሳ በኮሉ ቀበሌ ሊቀመንበር ተገድሏል። ባይሳ ገደፋ የተባለ የግንደበረት ወረዳ ነዋሪም በኦሮምያ ፖሊስ ተገድሏል። አብዛኞቹ ሟቾች ግን በመከላከያ ሰራዊትና በፌደራል ፖሊስ አባላት የተገደሉ ናቸው። ወጣት ፈቃዱ ድሪባ የአመያ ከተማ ነዋሪ ወላጆቹ 100 ብር ከፍለው አስከሬን እንዲወስዱ መገደዳቸውም በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
የሰብአዊ መብት ድርጅቱ በከፍተኛ ሁኔታ ቆስለው ሆስፒታል የተኙትን የ57 ሰዎች ስም ዝርዝር የያዘ ሲሆን፣ ድብደባ የተፈጸመባቸውን የ22 ሰዎች ዝርዝርም አስፍሯል። በእስር ላይ ከሚገኙት መካከል የ84፣ የደረሱበት ከማይታወቅ መካከል የ6 ሰዎችን ሙሉ ስምና አድራሻ ይፋ አድርጓል።
ይህ ሪፖርት በሚጠናከርበት ወቅት በምእራብ አርሲ በአጄ፣ ሻሸመኔ፣ ኮፈሌና አካባቢው፣ በምእራብ ወለጋ በአርጆና አካባቢው፣ በምእራብ ሸዋ አምቦና ጉዳር ህዝባዊ ተቃውሞው እንደቀጠለ እንደነበር ሰመጉ ገልጿል። የመንግስት ታጣቂዎች በአምቦ፣ በጀልዱና ግንደበረት አስገድዶ መድፈር መድፈር መፈጸማቸውን ነዋሪዎች ለድርጅቱ ገልጸዋል። ታጣቂዎች ሌሊት ሌሊት ቤት እያስከፈቱ ንብረት ይወስዳሉ፣ ድብደባ ይፈጽማሉ።
ሰመጉ በምእራብ አርሲ የኦሮቶዶክስ፣ የፕሮቴስታንትና የካቶሊክ አብያተ ክርስቲያናት መቃጠላቸውን ቢገልጽም፣ ድርጊቱ በማን እንደተፈጸመ አልገለጸም።

No comments:

Post a Comment