Wednesday, March 23, 2016

ወልቃት ጠገዴ ያሉ አዳዲስ መረጃዎች – ሙሉቀን ተስፋው

(ከቅራቅር፣ ከዳንሻና ሶሮቃ በስልክ ለማጣራት እንደሞከርኩት)
አንዲት እርጉዝ ሴት በትግራይ ልዩ ኃይል ፖሊስ ተደበደበች፤ ምን አደረግኩኝ ስትል ያረገዝሽ ወንድ ቢሆንስ! አሏት፡፡ ይህን የተናገረው አንድ ፖሊስ ሊሆን ይችላል፤ መቼም እየደበደበም ቀልድ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ግን እሳቤያችን እንዴት እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ ትናንት አንድ የ16 ዓመት ልጅ ዳንሻ ከተማ ተገድሏል፡፡
——
ዛሬ በቅራቅር ብዙ ሽሕ ሰዎች የተሳተፉበት ሰላማዊ ሰልፍ ተደርጓል፡፡ በሰልፉ የነበሩ መፈክሮች

‹‹የአንድ ፓርቲና የአንድ ብሔር የበላይነት ይቁም!፤ የኢትዮጵያ ሚዲያ የሕወሓት ብቻ መሆን የለበትም…›› ወዘተ የሚሉ ነበሩ፡፡ ሰልፉ መጨረሻ ላይ ጠገዴ ወረዳን አስተዳዳሪ ለማነጋገር የተሞከረ ቢሆንም ምክትል አስተዳዳሪው ‹‹ስለምን አርፋችሁ አትቀመጡም! እነርሱ ያሉት በትግራይ ክልል ነው፤ ይህ ደግሞ አማራ ክልል ነው›› የሚል መልስ ሰጥቷቸው ስብሰባው ያለ ስምምነት ፈርሷል፡፡
………
በወልቃይት ጠገዴ ሚሊሻ አባላት የሆኑ እስከ መጋቢት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ትጥቃችሁን አስረክቡ የሚል ማስታወቂያ ወጥቷል፡፡
——-
አንድ ጳጳስ ነኝ የሚል ሰው መስቀል ይዞ መጥቶ መንገድ እንዲከፍቱ የወልቃይትንና የጠገዴን ሕዝብ ልመና ቢያቀርብም ሕዝቡ ‹‹አንተ የትግራይ ገበሬ ነህ፤ የጵጵስና ልብስና መስቀል ተሰጥቶህ መጣህ እንጅ የየትኛው አገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንደሆንክ አናውቅክም፤ በዚያ ላይ በቀደም መስቀል የያዙ ሰዎች መጥተው እንዲሁ ለምነውን መንገድ ከከፈትን በኋላ ወጣቶቻችን ለቃቅመው አስረውብናል፤ ስለዚህ ይህን አንሰማም›› በሚል መልሰውታል፡፡
——-
ዳንሻ የታሰረ ሰው ብዛት ከ40 ይበልጣል፡፡ አቶ ሊላይ ብርሃኔን ያስያዘው ሾፌር ጎንደር ከተማ የታሰረ ቢሆንም በሕወሓት ትእዛዝ ተፈትቶ እንደሔደ ታውቋል፡፡ አቶ ሊላይ ብርሐኔ ግን የሱዳን ታርጋ ያላቸው መኪናዎች ገብተው ስለነበር ወደ ሱዳን ተወስዷል የሚል ግምት አለ፡፡ ወደ ሱዳን ከተወሰደ ደግሞ በሕይወት የመኖር እና ያለመኖር እድል አለው፡፡
—-
ነገ እስከ ከሰዓት ድረስ የሶሮቃ ኹመራ መንገድ ካልተከፈተ በመከላከያ ሰራዊት እርምጃ ይወሰዳል ተብሏል፡፡ ከጎንደር ጀምሮ የአርማጭሆና የቆላ ወገራ ሕዝብ ወደ ሶሮቃና አካባቢው በብዛት መሔዱን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡ ሶሮቃ ላይ የአማራ ክልል ልዩ ኃይል ወደ ዳንሻና ኹመራ የሚሻገሩትን ሰዎች ማገዱን ለማወቅ ተችሏል፡፡
—-
የግል አስተያየት፡
መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በመመለስ ወደ አላስፈላጊ እልቂት ዜጎች እንዳይገቡ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት፡፡ ይህን ከሕወሓት ግትር ባህሪ አንጻር መጠበቅ አስቸጋሪ መሆኑን አውቃለሁ፡፡ ሆኖም ግን ሕወሓት /ኢሕአዴግ መገንዘብ ያለበት ነገር ቢኖር አንድ ሰው በተገደለ አሊያም በታሰረ ቁጥር እልፍ ተቃዋሚ እንደሚነሳ ለመገንዘብ ሁልጊዜ የአስተሳሰብ ሕጻን ከመሆን መዳን አለበት፡፡ በእርግጠኝነት ግን በአስቸኳይ መንግሥት የሕዝቡን ጥያቄ በአገሪቱ ሕግ መሠረት መመለስ ካልቻለ በዜጎች ላይ የሚደርሰውን አደጋ ለመገመት አስቻጋሪ አይሆንም፡፡ ይህን መልእክት የምታነቡ አካላት ሁሉ ሕዝባችን ላይ በመንግሥት ወይም በገዥው አካል የታቀደውን ጥፋት ለመቀነስ መንግሥት ላይ ጫና ለማድረስ መረባረብ አለብን፡፡
‹ሥልጣን ካለው ሰው ኃይል ይልቅ የሕዝብ ኃይል ያሸንፋል››

No comments:

Post a Comment