Friday, March 4, 2016

በጎንደር‬ ከተማ ሲካሄድ የሰነበተው የፌደራል ፖሊሶች ስብሰባ ባለመግባባት ተበተነ

(አርበኞች ግንቦት 7 ድምፅ ሬዲዮ)  ፌደራል ፖሊሶች በጎንደር ከተማ ሳይንስ አምባ አዳራሽ ውስጥ ከየካቲት 21 2008 ጀመሮ ሲያካሂዱት የሰነበቱት ስብሰባ ምክትል ኮማንደር ሞላ ያስብ እና ምክትል ኢንሰፔክተር ታደስ አብርሃ በተባሉ የህወሓት ሰዎች ነበር የተመራው፡፡ ተሰብሳቢዎች እንዲወያዩበት የመድረኩ መሪ ከሆኑት ከእነኚህ የህወሓት ሰዎች የቀረበላቸው ሃሳብ “የፌደራል ፖሊስ ሰራዊት ስራ በቃን ማለትና የውጊያ ሞራል መላሸቅ” የሚል ነበር፡፡

በስብሰባው ላይ በርካታ ቅሬታዎች የተነሱ ሲሆን በተለይም ደግሞ ተደጋግሞ የሚወሳው በፌደራል ፖሊስ ተቋም ውስጥ የሰፈነው የህውሓት ሰዎች የበላይነት ዋነኛውና ሰፊ ጊዜ ወስዶ ያነታረከ የችግሩ ሰንኮፍ ነው፡፡
ህወሓቶች በሰራዊቱ ውስጥ በመንደር ተድራጅተው የበላይነት ከመያዛቸው በተጓዳኝ ፍፁም ቆራጭ ፈላጭ እና የለየላቸው አምባገነኖች መሆናቸው “በእንቅርት ላይ ጀሮ ደግፍ” እንደሆነባቸውም ጭምር ተስብሳቢዎች ተናግረዋል፡፡
ተደራራቢ ኃላፊነት ይዘው የወጣላቸው አምባገነኖች ከሆኑት የፌደራል ፖሊስ አዛዥ ከሆኑ የህወሓት ሰዎች መካከል ኮማንደር ካህሳይ በስብሰባው ላይ ስሙ ተነስቷል፡፡ ኮማንደር ካህሳይ የትራንሰፖርት ኃላፊ፣ የአጠቃላይ በጀት ኃላፊ፣ የወንጀል መከላከል ኃላፊ፣ የልዩ ገቢዎች ኃላፊ… እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
በስብሰባው ተሳታፊ የነበሩ አብዛኞቹ የፌደራል ፖሊስ አባላት በሰራዊቱ ውስጥ የሚታየውን የመንደርተኝነት መዋቅርና የዘረፋ መስመር የዘረጉት ኮሚሽነር ግርማይ ማንጁስ እና ረዳት ኮሚሽነር ተክላይ እንደሆኑ በመጥቀስ ከእንግዲህ ወዲህ ከህወሓቶች ጋር መስራት እንደማይፈልጉ አቋማቸውን አስታውቀዋል፡፡
በአጠቃላይ በጎንደር ከተማ ሳንይንስ አምባ አዳራሽ ሲካሄድ የሰነበተው የፌደራል ፖሊሶች ስብሰባ ከጭቅጭቅ፣ ንትርክና እርስበርስ ከመወነጃጀል የዘለለ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ በመሆኑም ባለመግባባት ተደምድሟል፡፡

No comments:

Post a Comment