Thursday, March 17, 2016

ዴቪድ ካሜሩን አቶ አንዳርጋቸው ጽጌን በማስመልከት ለኢትዮጵያ መንግስት ሁለት ጊዘ ደብዳቤ መጻፋቸው ተነገረ

ኢሳት (መጋቢት 8 ፥ 2008)

በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትን ያደርጋሉ ተብለው የሚጠበቁት የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ ሁለት ጊዜ ደብዳቤ መጻፋቸውን የሃገሪቱ መገናኛ ብዙሃን ሃሙስ ዘገቡ።
የሃገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሲያደርግ የቆየው ጥረት ውጤት አለማምጣቱን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደብዳቤውን እንደጻፉ በዝ ፊድ ኒውስ የተሰኘ ጋዜጣ አስነብቧል።

የብሪታኒያ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ወደሃገራቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ ለማመቻቸት በርካታ ጥረቶችን ሲያደርግ ቢቆይም የተፈለገው ውጤት ሊገኝ አለመቻሉን ሬፕሪቭ የተሰኘ የብሪታኒያ ድርጅት በድረ-ገጹ አስፍሯል።
የጥረቱን አለመሳካት ተከትሎች ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩን በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ያላቸውን ስጋት በመግለጽ ለጠቅላይ ሚኒስቴር ሃይለማሪያም ደሳለን ሁለት ጊዜ ደብዳቤ መጻፋቸውን ጋዜጣው የሃገሪቱን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዋቢ በማድረግ ዘግቧል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ በኢምባሲ ተወካዮች በቋሚነት እንደሚጎበኙ በተደጋጋሚ ማረጋገጫን ቢሰጡም የተገኘ ውጤት አለመኖሩን ጋዜጣው ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የተገኘን መረጃ ዋቢ በማድረግ በዘገባው አስነብቧል።
የብሪታኒያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ያደረገው ጥረት ውጤት አለማስገኘቱን አስመልክቶ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሩን ሪፖርት ሲያቀርብ መቆየቱም ታውቋል።
በቅርቡ በኢትዮጵያ ጉብኝትን የሚያደርጉት ዲቪድ ካሜሩን የአቶ አንዳርጋቸው ጽጌን ጉዳይ በማንሳት ከኢትዮጵያ ባለስልጣናት ጋር ውይይትን ያካሄዳሉ ተብሎ ይጠበቃል።
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት አስቀድሞ የሃገሪቱ ከፍተኛ የኢሚግሬሽንና የደህንነት ሃላፊዎች ከሁለት ሳምንት በፊት በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
የብሪታኒያው ጠቅላይ ሚኒስትር ለአቶ ሃይለማሪያም ደሳለኝ በጻፉት ደብዳቤም ሁለቱ ሃገራት ካላቸው የጠበቀ ግንኙነት አንጻር በአቶ አንዳርጋቸው ጽጌ ጉዳይ ዙሪያ ሲደረገ የቆየው ውይይት ፍሬ አለማፍራቱ ቅሬታን እንደፈጠረባቸው በደብዳቤያቸው አስፍረዋል።
ዴቪድ ካሜሩን ይህንን ጉዳይ ከአቶ አንዳጋቸው ጽጌ ቤተሰቦች ሲለዋወጡ መቆየታቸውንም ለመረዳት ተችሏል።

No comments:

Post a Comment