Friday, August 14, 2015

አንዳርጋቸውና ጓዶቹ

 ከአንተነህ መርዕድ
አምና ሰኔ 2006 ዓ ም አንዳርጋቸው ጽጌ በትራንዚት ላይ እያለ ከየመን በወያኔ መታፈኑ ሲነገር ሃዘንና ንዴት ያልተሰማው አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ ያለ አይመስለኝም። ወያኔ ኤርትራ ውስጥ እንዳለ ሊገድለው ያደረገውን ሙከራ ኢሳት በተከታታይ ስላቀረበው ምን ያህል አዳጋ ውስጥ እንዳለ ለሁሉም ግልፅ ነበር። የአንዳርጋቸው መያዝ ከታለመው ግብ በተፃራሪ አብዛኛውን ኢትዮጵያዊ ከዳር ዳር በቁጣ በማንቀሳቀሱ አፋኞቹ አምባገነኖች ከጠበቁት ውጭ ራሳቸውን ችግር ውስጥ ነው ያገኙት። መታፈኑ ለአስርት ዓመታት አፍዝዞ የያዘን ፍርሃትንና ክፍፍልን ሰባብሮ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ በጋራ እንዲቆም ከማድረጉም በላይ አንዳርጋቸው የደላ ኑሮውን ትቶ በረሃ ለበረሃ የተንከራተተለት፣ በርሃብና በበሽታ የተንገላታለት፣ ከጓዶቹ ጋር ለኢትዮጵያውያን ነፃነት ይበጃል ብሎ የደከመለት ግንቦት ሰባት በብዙ ኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ እንዲገባና የማይነጥፍ ድጋፍ ባልተጠበቀ ፍጥነት እንዲያገኝ ሲያደርግ የወያኔንና የመሰሎችን ጎራ ናዳ ልኮባቸዋል። በተለይም በክፍፍልና በፍርሃት ተሸብቦ የነበረው ውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ከወትሮው በተለዬ ዘላቂ ለሆነ ትግል ራሱን ማዘጋጀቱን በተለያዩ እንቅስቃሴዎቹ እያሳየ ሲሆን አገር ውስጥ በሰላማዊ ትግል ይሳተፉ የነበሩ በርካታ ወጣቶች ቁጭ ብሎ ከመታሰር በርሃ እያቆራረጡ ወደትግሉ መቀላቀላቸውና ሌላውም ህዝብ መነሳሳትን ማሳየቱን ወያኔዎችም ሊደብቁት አልተቻላቸውም።
አንዳርጋቸው የህይወት ተልዕኮውን በሚገባ ተወጥቷል። የግንቦት ሰባትን መሰረት ጥሏል። ከሌሎች ጋር ተባብሮ የመስራትን በር ከፍቷል። ከሁሉም በላይ የአንድ መሪ ሥራና ተልዕኮ አርዐያ መሆን ነውና በድፍረት በትግሉ ወላፈን ውስጥ ራሱን ማግዶ በማሳየቱ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያንን አነቃንቋል። ጠላቶቹም ሳይቀሩ ሊያከብሩት ያስገደደ ድርጊት ሆኗል። ዛሬ ወያኔ መጨበጫ አጥቶ እንደሚጨነቅ ሰሞኑን ቴዎድሮስ አድሃኖምን ማዳመጡ ብቻ በቂ ነው። አንዳርጋቸው በምን ሁኔታ ላይ እንዳለ ወያኔን የሚያውቅ ሁሉ ይረዳዋል። አንዳርጋቸው ችቦውን ለኩሶ ለተከታዩ ትውልድ አስተላልፏል። አንዳርጋቸው ከአሁን በኋላ መንፈስ ነው። ለጠላቶቹ የማይጨበጥ በጠባብ የወያኔ ጉላግ የማይታፈን የፅናት፣ የነፃነት መንፈስ። ጥላቻቸውንና ዘረኝነታቸውን ለመወጣትበጨለማ በሚያሰቃዩት አንዳርጋቸው ስም የሚታተም መጽሃፍ ሆነ ሌላ ቲያትር ዋጋ የለውም። ሚሊዮን አንዳርጋቸዎች ተንደርድረው በመግባት እሱን መስለውና እሱን አክለው ትግሉን ተቀላቅለዋል።

በዘንድሮው ሃምሌ ደግሞ ልክ በዓመቱ ትግሉን አምዘግዝጎ እጥፍ ድርብ በሚያሳድግ ሁኔታ በፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ወደ በረሃ መግባት ተደገመ። ትግሉ ይቀዘቅዛል ሲሉት ሞቀ፣ ይደክማል ሲሉት ጠነከረ፣ ይለሰልሳል ሲሉት ደደረ። የአንዳርጋቸው ስቃይ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ ያንገበገበ ቢሆንም የትግል ጓዶቹ የግንቦት ሰባት አመራሮች የገቡበትን እልህና ቁጭት ሃያልነት የሰሞኑ ድርጊታቸው ጉልህ ምስክር ሆኗል። ነዓምን ዘለቀ፣ ኤፍሬም ማዴቦና ሌሎችም አመራሮች እየተንደረደሩ መሬት ወርደዋል።(ምናለ ለዛሬ ብቻ የምወደውን ሄኖክ የሺጥላን መሆን በቻልሁ) ገጣሚ ባለመሆኔ ስሜቴን መግለፅ አልቻልሁምና ድሮ ከጎህ መፅሄት ካነበብሁት ለዚህ ሰሞን የሚመጥነውን ስንኝ መንፈሱን ብቻ እንዲህ ልበል
ጓድ እኮ ጓዱ ቢሞት
በትግል ሜዳ ላይ ቢቀጠፍበት
እዬዬ አይልም፣ አያለቅስም
ቁጭ ብሎ አያላዝንም
ይወርዳል፣ ይንደረደራል እንጂ በምትኩ ሺ ሊለቅም።
አዎ! ብርሃኑ፣ ነዓምን፣ ኤፍሬምና ሌሎችም ያደረጉት ይህንኑ ነው። ጓዳቸው ሲታሰርና ሲንገላታ ተቀምጠው ከንፈር አልመጠጡም፣ አላለቀሱም። ይልቅስ የጀመረውን ትግል መልካም ፍፃሜ ላይ ለማድረስ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ አንድ ህይወታቸውን ረክዘው መሬት ላይ ወርደዋል። የፋሲል የኔዓልምን አባባል ልዋስና “ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ የመስዋዕቱን ጣርያ ከፍ አድርጎ ሰቀለው” የሚለውን በሚገባ እስማማበታለሁ። ፈረንጆች እንደሚሉት “he shattered the ceiling” የመስዋዕትነቱን ጣርያ ሰበረው እንደማለት ነው።
ፕሮፌሰር ብርሃኑ በዚህ ድርጊቱ ትግሉን ከፍተኛ ደረጃ ከማድረሱም በላይ ጣምራ ተቀናቃኞቹን ማለትም ወያኔንና በተቃውሞ ጎራ ራሳቸውን መድበው ከእንቅፋትነት ውጭ ምንም የማይፈይዱ ከንቱዎችን ድንክ ነው ያደረጋቸው። ፀጥ ረጭ ነው ያሰኛቸው። እደገና ግጥም ፍለጋ ልባዝን። ጀግኖች አባቶቻችን አድዋ ላይ ጠላትን ድባቅ ሲመቱ ወገንን አላስጠጋ ያለውን የጣልያን መድፍ በወገን መድፍ አፉን የዘጋውን አባተ ቧ ያለውን እንዲህ ነበር ያሞገሱት።
አባተ ቧ ያለው ነገረኛ አዋሻኪ ሰው
ይህንን መድፍ ከዚያ መድፍ አቆራረጠው።
የብርሃኑ ወደ ትግል ሜዳ መግባት የዚያን መድፍ ያህል ጠላቱን ፀጥ ሲያደርገው የነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያውያንን ተስፋና ተነሳሽነት የትየለሌ ወደ ላይ ተኩሶታል። በአንዳርጋቸው መያዝ የተፈጠረው መነሳሳት በብርሃኑ ፋኖነት ወደ ሁሉን አቀፍ የድርጊት ትግል ተቀይሯል። በወያኔ ሚድያ፣በዌብሳይቶች፣ በፓልቶኮች፣ በባንኮኒ ዙርያ ለስርዓቱ ደጋፊዎችና አስመሳይ ተቃዋሚዎች ሳምባ ውስጥ ለጊዜውም ቢሆን አየር ጠፍቷል።
የትግሉ ሂደት (ፓራዳይሙ) ተቀይሯል። ወያኔ አንድ ነገር ባደረገ ቁጥር (አልሞትሁም ብዬ አልዋሽም ነው ያሉት) በስድት ወር መግለጫ በማውጣት አለሁ የሚለው ፖለቲካ ከሃያ ዓመት በላይ ኖረንበት አልፈየደምና አሁን ማብቃት አለበት። ሳምንት ሙሉ ሲለፋ ከርሞ ዲያስፖራው የሚያርፍባትን የሰንበት ሰዓቱንና ገንዘቡን ላልተጨበጠ ተረታ ተረት ማለቭ ሊያቆም ይገባል። የሚገደለው፣ የሚታሰረው፣ የሚደበደበው፣ የሚሰደደው ኢትዮጵያዊ ያለው ኢትዮጵያ ውስጥ ነው። የስደት መንግስትና ካቢኔ ማቋቋምም እቃቃ ጨዋታ ነው። አንድም መሬት ወርዶ መታገል ያለዚያም መሬት ላይ ያሉትን በሰላማዊ ሆነ በትጥቅ ትግል የሚፋለሙትን መርዳት እንጂ እዚህ በነፃው ዓለም ቁጭ ብሎ መስዋዕት እየከፈሉ ባሉት ላይ አቃቂር ማውጣት ሆነ በስማቸው መነገድ ጊዜው እያለፈበት ሄዷል።
የአብዛኛው ቅን ኢትዮጵያዊ ተግባርም የመከራውን ቀን ለማሳጠር ተግባራዊ ትግል በማድረግ ላይ ያሉትን አይዟችሁ ማለትና መደገፍ፣ ሲሳሳቱም በምክር ማስተካከልና ማጠናከር ነው። በስሜቱ በሚጫወቱና ሲጫወቱ በኖሩት ደጋግሞ መታለል አያስፈልግም። ድርጊታቸውን ሳይሆን ስምና አጀንዳቸውን ከጊዜው ጋር እየቀያየሩ ብቅ የሚሉትንም “እስቲ በተግባር እንያችሁና እንደግፋችሁ” ሊል ያስፈልጋል። በሰላማዊ ትግሉ ግንባራቸውን ሳያጥፉ ወህኒና ማእከላዊ የሚማቅቁ ጀግኖችንና ቤተሰቦቻቸውን መደገፍ አንዱ የትግል ግንባር ስለሆነ መታሰብና መከወን ያለበት ጉዳይ ነው። መከራውን የሚያሳጥረው ፕሮፌሰር ብርሃኑ እንዳለው እየተሰበሰቡ ማውገዝና መማማል ሳይሆን የተግባር እንቅስቃሴ ማድረግ ነው ። ትንንሿን የግል አቅማችንን ሳንንቃት ከሌሎች ጋር በማዳበል ጠጠሩ ሁሉ ወደ አንድ አቅጣጫ ማለትን የወያኔን የጨለማ አገዛዝ ለማስወገድ ወደሚደረግ የትግል አቅጣጫ መወርወር እንጀምር።
አንድ ህይወታቸውን ለአገር በሰጡት ወገኖች ላይ የሚሰነዘረውን ማንኛውንም አይነት የጎንዮሽ ደባ ማጋለጥና እረፉ ማለት የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ ነን። ጊዜው ሰከን ብለን እየተደጋገፍን ወደ አንድ አገራዊ አቅጣጫ ለመሄድ የምንንቀሳቀስበት እንጂ እየተጠላለፍን ስንድህ የምንኖርበት አይደለም።
እግዜብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ!

No comments:

Post a Comment