Monday, August 24, 2015

በነባሩና በአዲሱ የድርጅቱ አመራር መካካል ልዩነት መኖሩን ብአዴን ገለጸ

ነኅሴ ፲፰ (አስራ ስምንት) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ድርጅቱ በ11ኛው ድርጅታዊ ጉባኤ ላይ እንደገለጸው፣ ለረጅም ጊዜ በአመራርነት ቆይቶ ስልጣኑን በመተካካት ሂደት ባስረከበውና ቁልፍ ስልጣኑን በተረከበው መካካል የመግባባት ችግር መኖሩን ገልጿል።ነባሩ አመራር ሁሉንም ሃላፊነት አስረክቦ ድርጅቱን የመልቀቅና ራሱን ገለል አድርጎ ለመኖር ይፈልጋል ያለው ብአዴን፣ በዚህም ላይ ነባሩ አመራር በአዲሱ አመራር እንደማይረካና ተደጋጋሚ ቅሬታ እንደሚያቀርብም ገልጿል።

ቁልፍ ስልጣን የተረከበው አዲሱ አመራርም የራሱን አቅም የማያውቅ፣ ስልጣኑን ካስረከበው ነባር አመራር ለመማር ፍላጎት የሌለው ነው ብሎአል።
በአዲሱ እና በነባሩ አመራር በኩል ለታየው አለመግባባት ምንጩ ዲሞክራሲያዊ ትግል አለመጎልበት፣ አድባርይነት ፣ ፊት ለፊት ለመታገል አለመፈለግ፣ ድክመቶችን ለመቀበል ፍላጎት አለመኖር፣ ሂስና ግለሂስን አለመቀበልና የድርጅቱን አሰራሮችን በተግባር ለማዋል ፍለጎት አለማሳየት ናቸው ብሎአል።
በቅርቡ ቁልፍ የሃላፊነት ቦታዎችን በተረከበው አመራርና በቆየው አመራር መካከል መደጋገፍ የሰፈነበት ግንኙነት ካልተፈጠረ መተካካቱ ህይወት አይኖረውም ብሎአል።
በአዲሱ አመራርና እና ሃላፊነቱን ባስረከበው አመራር መካካል የታየው ልዩነት፣ ነባር አመራሩ የመተካካት መርሆ ከነባራዊ ሁኔታዎች ጋር እንዲዛመዱ እየጠየቀ ነው። ምንም እንኳ አቶ በረከት ስምኦን በ11ኛው የድርጅቱ ጉባኤ ከስራ አስፈጻሚነት ቦታቸው እንደሚነሱ ቢታወቅም፣ ከዚህ ቀደም በተገለሉት በእነ አቶ አዲሱ ለገሰ፣ ተፈራ ዋልዋ እና ሌሎችም አመራሮችና በአዲሱ አመራር መካካል የተፈጠረው ክፍተት ስጋት ላይ ሳይጥላቸው አይቀርም። አዲሱ አመራር ነባሩን አመራር የሚንቀው ሲሆን፣ ነባሩ አመራር ደግሞ አዲሱ አመራር የትግል ወኔ የለውም ሲል ይተቻል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ብአዴን በተለያዩ ክልሎች እና በውጭ አገር የሚገኙ የአማራ ተወላጆችን ለማደራጀት ያደረገው ሙከራ መክሸፉን አስታውቋል። በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ የክልሉ ተወላጆች የድርጅቱን አስተሳሰብ እንደማይደግፉና ተወላጆቹን ለማደራጀት ቀደም ብሎ ያደረጋቸው ሙከራዎች መክሸፋቸውን አስታውቋል።

No comments:

Post a Comment