Wednesday, August 5, 2015

የቃሊቲ ማረሚያ ቤት ለ3ኛ ጊዜ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ፍርድ ቤት ሳያቀርብ ቀረ

ሐምሌ ፳፱ (ሃያ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለተከሰሱት 2ኛ ተከሳሽ አቶ አሸናፊ አካሉ ፣3ኛ ተከሳሽ አቶ ደናሁን ቤዛ ፣4ኛ ተከሳሽ አቶ ምንዳዬ ጥላሁን እና 5ኛ ተከሳሽ አቶ አንሙት የኔዋስ የመከላከያ ምስክር ሆነው አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ለዛሬ ሀምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. ፍርድ ቤት እንዲያቀርብ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የደረሰው የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡

ተከሳሾቹ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን በመከላከያ ምስክርነት እንዲቀርቡላቸው የጠየቁት የፌደራል አቃቤ ህግ ፣ አንዳርጋቸው ፅጌና ከሌሎቹ የድርጅት አመራሮች ጋር በአካልና በሌሎች የመገናኛ ዘዴዎች በመገናኘት ስለ ሽብር ተግባሩ አፈፃፀም በመግባባት፣ ኤርትራ ወደሚገኘው የግንቦት ሰባት ካምፕ ሄደው ስልጠና በመውሰድ፣ ተልዕኮ ተቀብሎ ወደ ሀገር ውስጥ በመመለስ የሚል ክስ ስለመሰረተባቸው ነው፡፡
የልደታ ፍርድ ቤት አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ በዘመነ ካሴ የክስ መዝገብ ከ2ኛ እስከ 5ኛ ለሚገኙት ተከሳሾች ሀምሌ 13 ቀን 2007 ዓ.ም. ልደታ ፍርድ ቤት ቀርበው ምስክርነት እንዲሰጡ ወስኖ የነበር ቢሆንም፣ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት የሚላከው ማዘዢያ እንደዘገየ በመግለጽ ለሀምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ቀጠሮ መስጠቱ ይታወቃል፡፡

ሆኖም አቶ አንዳርጋቸው ሀምሌ 15 ቀን 2007 ዓ.ም. ያልቀረቡ ሲሆን፣ ማረሚያ ቤቱ ትዕዛዙ ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት መጻፍ ሲገባም ለአዲስ አበባ ማረሚያ ቤት ተብሎ ስለተጻፈ ማቅረብ እንዳልቻለ ገልጿል።
ፍርድ ቤቱም ማዘዢያው ለቃሊቲ ማረሚያ ቤት ተብሎ እንዲፃፍ አዝዞ ለሶስተኛ ጊዜ ማረሚያ ቤቱ ለሀምሌ 29 ቀን 2007 ዓ.ም. አቶ አንዳርጋቸውን እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡ ይሁን እንጅ በዛሬው ዕለትም የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ሳያቀርብ ቀርቷል፡፡
የልደታ ፍርድ ቤት 19ኛ ወንጀል ችሎት የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ እንዲያብራራ፣ እንዲሁም በዛው ቀን ለምስክርነት እንዲያቀርብ ሲል ለጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ለአራተኛ ጊዜ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
ተከሳሾቹ አጭር ቀጠሮ ተሰጥቶ የቃሊቲ ማረሚያ ቤት አቶ አንዳርጋቸውን ለምን እንዳላቀረበ ማብራሪያ እንዲሰጥ ቢጠይቁም፣ ፍርድ ቤቱ በሌሎች መዝገቦች የሚሰሙ ምስክሮች ስላሉና ከነሀሴ15 ቀን 2007 ዓ.ም በኋላ ፍርድ ቤት ስለሚዘጋ በሚል ምክንያት አቤቱታቸውን አልተቀበለውም፡፡
በሌላ በኩል በማረሚያ ቤትና በፍርድ ቤቱ ችግር አቶ አንዳርጋቸውን ለምስክርነት ማቅረብ ባለመቻሉ እየተጉላሉ መሆናቸውን ተከሳሾቹ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡7ኛ ተከሳሽ ም/ኢንስፔክተር ሙልዬ ማናዬ ‹‹የአድራሻ ለውጥን ሰበብ አድርጎ በሚቀርብ ተልካሻ ምክንያት ለምን እንጉላላለን? እኛ ፍትህ ፈላጊ ነን፡፡ቃሊቲና ቂሊንጦ በአንድ ደቂቃ የስልክ ግንኙነት መገናኘት እየቻሉ በቀጠሮ እየተጉላላን ነው›› ያሉ ሲሆን፣ ‹እኔ የመከላከያ ምስክሬን ያቀረብኩት የዛሬ ዓመት ነው፡፡ለእኔ ብለው ቤተሰቦቼ በሬያቸውን ሸጠዋል፡፡ግን አሁንም ድረስ እየተጉላላሁ ነው፡፡ቤተሰቦቼ አሸባሪዎች ናቸው ተብለው ቤት የሚያከራያቸው አጥተዋል፡፡ልጆቼ በረንዳ ላይ ወድቀዋል፣ቤተሰባችን ተበትኗል፡፡ ምስክሩን ማቅረብ ካልቻሉ ለምን ክሱን ውድቅ አታደርጉትም?›› ሲሉ የፍርድ ሂደቱ በመጓተቱ እየደረሰባቸው የሚገኘውን በደል መናገራቸውን ነገረ-ኢትዮጵያ ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment