Wednesday, November 25, 2015

በኦሮሚያ ክልል በምስራቅና ምዕራብ ሃረርጌ በአርሲ ዞኖች የተረጂዎች ቁጥር አሻቀበ

ኢሳት ዜና :-በኢትዮጵያ የተከሰተው አስከፊ ድርቅ አድማሱን እያሰፋ ሲሆን በኦሮሚያ ክልል በምዕራብና ምስራቅ ሃረርጌ ዞኖች ውስጥ የሚገኙ አፋጣኝ የምግብ ዕርዳታ ፈላጊዎች ቁጥር በአሁኑ ወቅት 50 በመቶ በላይ ማሻቀቡን የምሥራቅ ሐረርጌ ዞን የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሃረን አልዪ ለሪፖርተር ገልጸዋል።

እስካሁን ድረስ ከ549 ሽህ ተረጂዎች ተለይተው ዕርዳታ ሲሰጣቸው የቆየ ቢሆንም ድርቁ አሁንም ለውጥ ሳያሳይ በመቀጠሉ የተረጂዎች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን በምሥራቅ ሐረርጌ ዞን ብቻ ከ320 ሺሕ በላይ ተጨማሪ ተረጂዎች የመንግሥትን ዕርዳታ የሚሹ በመሆናቸው፣ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ የተረጂዎች ቁጥር ከ900 ሺሕ በላይ ይደርሳል ተብሎ ተገምቷል፡፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞንም ከ500 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የዞኑ ነዋሪዎች ዕርዳታ ሲሰጣቸው የነበረ ቢሆንም አሁንም ድርቁ እየሰፋ በመምጣቱ አሃዙ አሻቅቦ ከ720 ሺሕ በላይ የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች አፋጣኝ የምግብ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና በሁለቱም ዞኖች እስካሁን ዕርዳታ ሲሰጣቸው የነበሩት የባሰ ችግር የነበረባቸው ሲሆኑ ድርቁ እየተራዘመ በመምጣቱ ግን የተሻሉ ናቸው የተባሉትንም ጭምር በአሁኑ ወቅት አፋጣኝ ዕርዳታ እንደሚያስፈልጋቸውና በድርቁ ሳቢያ የውሃ ዕጥረት በመከሰቱ ሁኔታውን የከፋ አድርጎታል ሲሉ አቶ ሃረን አልዪ አክለው ገልጸዋል።
በምዕራብ ሐረርጌ ሚኤሶ ወረዳ አርሶ አደሮችና አርብቶ አደሮች፣ እንዲሁም በምሥራቅ ሐረርጌ በድርቅ የተጎዱ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት የሚደረግላቸው ዕርዳታ በቂ ያለመሆኑ ብቻ ሳይሆን፣ ጨርሶ ዕርዳታ እየተሰጣቸው አለመሆኑንና የሚሰጣቸው ዕርዳታ ባለመኖሩም አንዳንዶቹ የትውልድ ቀያቸውን በመልቀቅ ወደ ጂቡቲና ወደተለያዩ አካባቢዎች ለመሰደድ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡ቀሪዎቹ በበኩላቸው ከአዲስ አበባ ጂቡቲ በተዘረጋው የባቡር ፕሮጀክት ላይ በቀን ሠራተኝነት ተቀጥረው በቀን 30 ብር እየተከፈላቸው ሕይወታቸውን ሲመሩ ከዚህ ሲብስም በደህናው ጊዜ ያደለቧቸውን ከብቶች እየሸጡ ነው፡፡
በተጨማሪም በኦሮሚያ ክልል በአርሲ ዞን ዶዶታ ወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎችም ከብቶቻቸው በድርቁ ምክንያት ስለተጎዱና ከችግር ለማምለጥ ለመሸጥ ወደ ገበያ ሲያወጧቸው ዋጋ እየወደቀባቸው መቸገራቸውን፣ ሲብስም ቀድሞ እስከ 20 ሺሕ ብር ይሸጡ የነበሩትን ከብት ከአምስት ሺሕ ብር ባልበለጠ ዋጋ ለመሸጥ መገደዳቸውን ይናገራሉ፡፡
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ሚኤሶ ወረዳ ብቻ እስካሁን ከ2 ሺ 200 በላይ ከብቶች በድርቁ ሳቢያ የሞቱ ሲሆን ተማሪዎች ትምህርታቸው በርሃብ ምክንያት ለማቋረጥ ተገደዋል፡፡ አንድ አርሶ አደር የድርቁን ሁኔታ ሲያስረዱ የልጆቻችን ሰውነት ቀንሷል ከትምህርት ቤትም እየቀሩብን ነው ለውኃ ችግር መፍትሔ ካልመጣ አካባቢውን ለቆ መሄድ ግድ ይሆንብናል። ይህ የፈጣሪ ጉዳይ ስለሆነ ከዘራነው አላገኘንም፡፡ ከፈጣሪ በታች ያለን መንግሥት ነውና ዕርዱን ብለናል።
በተደጋጋሚ ወደ አካባቢው የሚመጡት የመንግሥት ኃላፊዎች ችግሩን ሰምተው ይሄዳሉ እንጂ ዕርዳታ እያደረጉልን አይደለም፣ በማለት መንግስት ከጎናቸው ሆኖ ለችግራቸው እንዳልደረሰላቸው በምሬት ተናግረዋል።በዕርዳታ አሰጣጥ ላይ መድሎና ሙስና መኖሩንም የዞኑን ባለስልጣናትና የአካባቢውን ነዋሪዎችን ጠቅሶ ሪፖርተር ዘግቧል።

No comments:

Post a Comment