Thursday, November 19, 2015

የብአዴን ታጋዮች የሞትንለት እና የደማንለት ድርጅት አክስሮናል አሉ፡፡

ኀዳር ፱ (ዘጠኝ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ብአዴን ህዳር 11 በባህርዳር በሚያከብረው በአል ላይ ለነባር ታጋዮች ልዩ የሽልማት ስነስርዓት ያዘጋጀ ሲሆን፣ ለሽልማቱ የታጩት አመራሮች በድርጅት ነባር አባላት አስተያየት እንዲሰጥባቸው ማድረጉን ተከትሎ፣ ነባር ታጋዮቹ በብአዴን አመራሮች ላይ የሰላ ትችት አቅርበዋል፡፡ ታጋዩች ከድል በሁዋላ እስከ ሜጀር ጀኔራልነት የሚደርስ ማዕረግ ቢሰጠንም ከመዝገብ ቤት ያለፈ የውሳኔ ሰጭነት ስልጣን የለንም ብለዋል፡፡

ነባር አባሎቹ “ብአዴን እስከዛሬ ረስቶን ዛሬ ‘ለመስዋዕትነታችሁ ምስጋና እና ሽልማት አዘጋጅቻለሁ’ የሚለን፣ ከህወሃት በደረሰበት ተፅኖ እና በህወሃት አርባኛ አመት አከባበር ቅናት ውስጥ ስለወደቀ ነው ፣ እኛ ከህወሃት ታጋዮች ያነስን ነን።” ማለታቸውን በግምገማው የተገኘችው ወኪላችን ገልጻለች።
“የታገልንለት አላማ ግቡን ስቷል” ያሉት ታጋዩች፣ አሁን ያሉት ግንባር ቀደም መሪዎች እንዴት ስልጣኑን በጉልበት እንደነጠቋቸው በድፍረት ተናግረዋል፡፡” ተገፍተን ወድቀናል” የሚሉት ነባር ታጋዮች፣ “ፓርቲው ጉልበት የሌለው ተጋዩችን ያልታደገ ድርጅት ነው” ሲሉ አማረዋል፡፡
“እኛ የፈጠርነው ኦህዴድ እና እኛ ያቆምነው ደህዴን የብአዴን ውልድነቱን ክዶ፣ በ40 ኛው የህወሃት በዓል የአማራን ህዝብ ውለታ ክዶ ለጉልበተኞች ሲያድር፣ እኛ ምን ላይ ነን? እኛ ስማቸውን የቀየርነው ጌታቸው ጀቤሳና ሌሎች ታጋዮች በህውሃት እንዲባረሩ ያደረገ ድርጅት ፣ ህላዌ ዮሴፍ፤ መዝሙር ፈንቴ፣ ተፈራ ሃይሉና ካሳ ተክለብርሃንን ይዞ ለአማራ ህዝብ ምን እንደሚያመጡ እስኪ ንገሩን?” ሲሉ በቁጣ ጠይቀዋል፡፡
ለውጥ ያመጡ የብአዴን ወጣት መሪዎች ታፍነዋል ያሉት ተሰብሳቢዎች፣ ያለ ውሳኔ የታሰሩትን የገቢዎች ዋና ባለስልጣን የነበሩትን አቶ መላኩ ፈንታን በምሳሌነት አንሰተዋል፡፡
“የደህንነቱን እና ፋይናንስ ሚንስትርነቱን ህውሃት በያዘበት ሁኔታ ተቀዳሚ ም/ጠቅላይ ሚንስትር ብአዴን ነው ብሎ መናገር ሞኝነት ነው ሲሉ በተሰጣቸው መልስ ላይ ያፌዙት አባላቱ፣ በዚህ ከቀጠለ አማራው በማዕከላዊ መንግስት ውሳኔ ላይ ተሰሚነት እና ፈፃሚነት አይኖረውም ብለዋል ፡፡ ከድርጅቱ የለቀቁ ነባር ታጋዮች ይሸለሙ አይሸለሙ በሚለው ዙሪያም ሰፊ ክርክር ተካሂዷል። በትግሉ ወቅት ሃይል 21- ይመሩ የነበሩ ከኮማንደር አዲሱ ጋር ያዋጉ ሃይሎች፣ ምክትል ኮማንደር አስራደና ኮሚሳር ሞገስ ሸጋው በምስጋናው መረሳታቸው ሌላው ያጨቃጨቀ ጉዳይ ነበር። የመጀመሪያዎቹ የካድሬ አሰልጣኞች ተመስገን አበበ፣ ሞገስ ሸጋው፣ ታሪክ ፈንቴ፣ ሰለሞን ታደሰ፣ ጥላሁን ገብሬ ተረስተዋል በሚልም ስማቸው ተነስቷል።
እንዲሁም ኢህዴን የመጀመሪያዋን ክፍለ ጦር ላብአደር ብሎ በሰየመበት ጊዜ ድርጅት ሃላፊ የነበረው አበራ ተክለዮሃንስ፣ ሎጂስቲክስ ሃላፊው ጥጋቡ ታመነ ፤ የኢህዴን የሴቶች ኮሚቴ አባላት የነበሩት ነፃነት አበራ ፣ ሙሉ ግርማይ፣ ምስራቅ ማሞ፣ ፍሬህይወት አያሌው፣ እንወይ ገብረመድህን፣ ካስወይ መስፍን ፣ የኢታሴማ አመራር በመሆን በኮንፈረንሱ የተመረጡት ነፃነት፣ ገነት፣ ሙሉ፣ ፍሬህይወት፣ እንወይ፣ ምስራቅ ማሞ፣ አሰፋሽ መረሳታቸው የብአዴን አባለቱን አበሳጭቷል።
ከሰቆጣ ከተማ ማዘር /ብርሃኔ አበራ/፣ ከአምደወርቅ እማማ ምንትዋብ፣ ከበለሳ ደግሞ አምበል ለአብነት ያህል የሚጠቀሱት ተርሰተዋል በሚል በባለስልጣነቱ ላይ ወቀሳ አቅርበዋል። “አሁን ያለው የመልካም አስተዳደር ችግር ስርዓቱን እንዳይንደው ተጠንቀቁ፣ ለስሙ ወንበር ላይ ተቀምጣችሁዋል ውሳኔው የሚሰጠው ግን ሌላ አካል ነው ” በማለት አስተያየት የሰጡም ነበሩ ብአዴን ባለሃብቱ የገንዘብ መዋጮ እንዲከፍል ማስገደዱ አሁንም ነጋዴዎችን አስመርሯል።
በሌላ ዜና ደግሞ በክልሉ የሚታየው ከድርቁ ጋር የተያያዘው ችግር በቀጣዮቹ ወራት መንግስት ሊቆጣጠረው ወደ ማይችልበት ደረጃ ይደርሳል ሲሉ ነዋሪዎች ስጋታቸውን ገልጸዋል።
ሰሜን ወሎ እና ዋግ ህምራ ዞኖች ህዝቡ በከፍተኛ ሁኔታ ተርቡዋል፡፡የመንግስት አመራሮች ህዝቡን በአለበት አቁሙት የሚል ቀጭን ትዕዛዝ ለካድሪዎች አሰተላልፈዋል፡፡
እስካሁን በርሃቡ ምክንያት 36 የመጀመሪያ ደረጃ የገጠር እና 8 የከተማ ትምህርት ቤቶች ተማሪ አልባ ሁነዋል፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ስራ ፍለጋ መሰደድ ጀምረዋል።
በድርቁ የተነሳ ወደ አዲስ አበባና ባህርዳር ሰዎች መሰደድ መጀመራቸውም ታውቋል። የነገረ ኢትዮጵያ ሪፐርተር በአዲስ አበባ ልመና የጀመሩ የሰሜን ሰዎችን ፎቶ ግራፍ በማንሳት የችግሩን አስከፊነት አሳይቷል።
በአዲስ አበባ አንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ደግሞ አንድ ተማሪ ” እራበኝ እናንተስ?” የሚል ጥቁር ሰሌዳው ላይ ጽፎ ተገኝቷል።

No comments:

Post a Comment