Monday, November 30, 2015

በሃረሪ ፖሊስና መከላከያ መካከል በተፈጠረው ግጭት ሃረር ሰላም አጥታ ሰነበተች

ኀዳር ፳ (ሃያ) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በከተማዋ ውጥረት ነግሶ መሰንበቱን የገለጸው ወኪላችን፣ መንስኤውም አንድ የመከላከያ ሰራዊት አባል ተደብድቦና በጥይት ተመትቶ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት መሆኑን ተከትሎ ነው።

ውጥረቱን ተከትሎ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ትራፊክ ዋና አዛዥ ኮማንደር አብዲ ኢብራሂም የተሰወሩ ሲሆን፣ በመከላከያ ሰራዊት አባላት በጥብቅ እየተፈለጉ ነው። ጉዳዩን ለማጣራት የመከላከያ ሚኒስትሩ ሲራጅ ፈርጌሳና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር በከተማዋ የተገኙ ሲሆን፣ የክልሉ መንግስት መከላከያ ፈጸመብኝ ያለውን 18 ክሶች ሲያቀርብ መከላከያ በበኩሉ የክልሉ ፖሊስ ፈጸመብኝ ያለውን 12 ክሶች አቅርቧል።
ሁለቱ ባለስልጣናት የክልሉን መንግስት ጥፋተኛ ነው ብለው የደመደሙ ሲሆን፣ በዚህም የተነሳ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አብዱል ፈታህ አብዱልቃድር ከስልጣናቸው እንዲነሱና ኮማንደር አብዲ ደግሞ ከስልጣናቸውና ከፖሊስ አባልነትም ጭምር እንዲባረሩ ከመደረጋቸውም በላይ ለወደፊቱም በየትኛውም የመንግስት ስራ እንዳይቀጠሩ ተወስኖባቸዋል።
መከላከያም አስፈላጊውን የሰው ሃይል በማሰማራት ኮማንደር አብዲን እንዲይዝ ትእዛዝ ተላልፎለታል። ጉዳት የደረሰበት መከላከያ ሰራዊት አባል በምስራቅ እዝ የመጀመሪያ ህክምና ከተደረገለት በሁዋላ ፣ ለከፍተኛ ህክምና ጦር ሃይሎች ተልኳል።
ክልሉ በተባረሩት ፖሊስ ኮሚሽነር ቦታ አቶ ነስሩ አሊ ተሹመዋል። በኮማንደር አብዲ ኢብራሂም ቦታ ደግሞ አቶ አብዱል ፈታህ ተሹመዋል።
ከሃረር ዜና ሳንወጣ፣ የመብራትና እና ውሃ ችግር የከተማውን ህዝብ አስመርሯል። የከተማው ነገዴዎች መንግስት ከፍተኛ ግብር እንደጣለባቸው፣ ይሁን እንጅ መብራት በወጉ እንኳ ባለማግኘታቸው ስራቸውን ለመስራት አለመቻላቸውን ገልጸዋል።
በአንዳንድ አካባቢዎች ህዝቡ ፊርማ አሰባብሶ ቢያስገባም መልስ አላገኘም።

No comments:

Post a Comment