Friday, November 27, 2015

አንተም ደመቀ መኮንን! (ከአንተነህ መርዕድ)

ከአንተነህ መርዕድ
Demeke Mekonnen Hassen Deputy Prime Minister of Ethiopia
መጥኔ በሁለመናው ለተራብነው!!
ይድረስ ለማውቅህና ለማታውቀኝ የኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን
የኢትዮጵያ ህዝብ እስከአሁን መሪዎቹን መርጦ አያውቅም። ሁሉም በጉልበት ትክሻው ላይ ተፈራርቀው ወጥተውበታል፤ እየተካኩም አሁን ላለበት ከዓለም የመጨረሻነትና የርሃብ ተምሳሌትነት አድርሰውታል፤ አድርሳችሁታል። ያለፈ ታሪክ እየቆፈርን ማን ምን ሠራ እያሉ ለመዘባነን በአሁኑ ወቅት ህሊና ላለው አንገብጋቢ ጥያቄ አይመስለኝም። በእጃችን ላይ ያለውን ዐይኑን አፍጥጦ የመጣውንና የብዙ ሺዎችን ህይወት ለመቅጠፍ “ሀ’’ ብሎ የጀመረውን ርሃብ ለመግታት ደመኛ ጠላቶችም ቢሆኑ የሚተባበሩበት ወቅት ነውና። ከየትም ወገን ይምጣ ርሃብን ለፖለቲካ ፍጆታ የመጠቀምን ያህል ጭካኔ ከቶ የለም።

ክቡር ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር! ሰሞኑን መንግስትህን ወክለህ ስለርሃቡ የሰጠኸው መግለጫ አጥንቴ ድረስ ተሰምቶኛል። ማንነትህንና ምንነትህን አጥርቼ የማውቅ ቢሆንም ይህን ያህል ወርድህ በርሃብተኛው ትሳለቃለህ ብዬ አልጠበቅሁም ነበር። በኃይለስላሴ የመጨረሻ ዘመን ርሃብ በጨካኝ እጁ ሰሜን ኢትዮጵያን ሲገርፍ፤ የቻለ ቤተሰብና የቀረች ንብረቱን፣ ያልቻለም ውሃ መጠጫ ቅሉን አንጠልጥሎ በመላ ኢትዮጵያ ነፍሱን ለማዳን ተሯሩጧል። ገና ልጅ ሁኜ ርሃብና መንገድ ያደከማቸው አዛውንት፣ አሮጊት፣ ጎልማሶችና ህፃናት ጎጃም ውስጥ መተከል አውራጃ ለመስፈር ሲሄዱ የነበራቸውን ድካምና እንግልት ዐይቻለሁ። የሚያልፉት በአካባቢዬ ነበርና ትዝታዬ ህያው ነው። እነዚህ ምስኪኖች ድክሟቸው ባረፉበት ሄጄ ከእኩዮቼ ጋር የተጫወትሁት አሁንም ድረስ አይጠፋኝም።
ውድ ደመቀ መኮንን! እኒያ ርሃቡ ካደከማቸውና ጣመኑ ከመታቸው በመንደሬ ተስተናግደው ካለፉት ጎልማሶች አባትህ አቶ መኮንንና ቀሪው ቤተሰብህ እንዳሉበት በእርግጠኝነት እናገራለሁ። ከወሎ መተከል ቻግኒ ያለውን ርቀት ዛሬ በምትንፈላሰስበት ላንድ ክሩዘር ፍጥነት አትለካው። ቤተሰብህ ያንን ሁሉ መንገድ ለሳምንታት በመጓዝ አቋርጠው መተከል መንታወሃ አካባቢ ጫካ መንጥረው በመስፈር፤ በለሙ መሬት ሰርተው፤ ርሃባቸውን አስታግሰው፣ የአካባቢውን ገበያም አጥግበዋል። እየቆዩም በመደላደል ቤተሰቦቻቸውን አምጥተዋል። ይህ ሁሉ ሲሆን ነገሩ ሁሉ አልጋ በአልጋ አልነበረም። ዛሬ አንተና አለቆችህ አይዞህ እያላችሁ በዘረኝነት የቀሰቀሳችኋቸው አዲሶቹ ዘረኛ ካድሬዎች ሠርቶ የሚበላውን ተፈናቃይ ሃያና ሰማንያ እየገደሉ መቅበራቸውን ሰሞኑን በዜና እንደሰማነው ሁሉ፤ በጊዜው አጠራር ሻንቅላ አሁን ደግሞ ጉምዝ የሚባለው አዳኝ ህብረተሰብ በዚያን ጊዜም ሰፋሪዎችን ሳያስቡ ዘምቶባቸው ብዙዎችን በጥይት፣ በቀስትና በገጀራ ጨፈጨፋቸው።
ርሃቡ ያጠቃቸው የወሎ ተሰዳጆች ወደ መተከል ሲሄዱ ሰውነታቸው ቢደክምም በተስፋ ነበር። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ጭፍጨፋ ሲፈፀምባቸው ለማምለጥ የቻሉት ሰፈራችን ሲደርሱ ግን ስለሞቱ ቤተሰቦቻቸው እያለቀሱ ይናገሩ የነበረው አሁንም ልቤ ውስጥ ህያው ሆኖ ይኖራል። እነዚያ አብሬ የተጫወትሁት እኩዮቼና አዛውንቱ ማምለጥ አልቻሉም። ደርግ፣ ወያኔ ሆነ ቀሪው ህዝብ ያወግዛቸው የነበሩት ንጉሥ ፈጥኖ ደራሽ ሰራዊት በመላክ፣ አመፀኞችን በመቅጣት፣ ሰፋሪዎች ተመልሰው ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ አስችለዋል። አንተም የዚያ ስቃይና በኋላም የተፈጠረው መረጋጋት ውጤት ነበርህ።
አቶ ደመቀ መኮንን ይህንን ሁሉ የምዘረዝረው ቀሪው ኢትዮጵያዊ እንዲያውቀው እንጂ አንተማ አታውቀውም ብዬ አይደለም። ይህንን እውነት ለማወቅ ከፈለግህ መተከል መንታውሃ ውረድና በህይወት ያሉትን አባትህን፣ አጎቶችህንንና አክስቶችህን ከዚያ መራራ ትዝታ ጋር እንዴት እንደኖሩ ጠይቃቸው። በዝርዝር ይነግሩሃል። አንተማ ምን ህሊና ኖሮህ ታስታውሰዋለህ! ርሃብን በተመለከተ፣ ድርቅንና ስደትን ከእሱም ጋር ተያይዞ የሚመጣውን ጨካኝ ሞት በተመለከተ ህያው ምስክር ትሆናልህ ብለው ሲያስቡ፤ በርሃብ ማትረፍና መዝረፍ የለመደው ስርዓት ጠበቃ ሆነህ ሲያዩህ አባትህ አቶ መኮንን፣ መላው ዘመዶችህ፣ እነ አያ ሙሄ፣ እነ ዘይነባ ምን ያህል ያፍሩብህ?
ደመቀ እባክህ ህወሃትን በተለይም መለስ ዜናዊን የማደንቅበትን ብቸኛ ነገር ላካፍልህ። እቃ ፈልጎ የማግኘትን ችሎታ የት እንደተካኑት ጠይቀኻቸዋል? ይህንን ብቃታቸውን ያስመሰከሩበትን ልዘርዝርልህ። ሲጀምሩ ታንምራት ላይኔን፣ ተፈራ ዋልዋን፣ አዲሱ ለገሰን፣ አባዱላ ገመዳን፣ኩማ ደመቅሳን፣ ካሱ ኢላላን ቆይቶ ክፍሌ ወዳጆን፣ ዳዊት ዮሃንስን፣ ገነት ዘውዴን ወዘተ…ፈልገው በማግኘት አስከፊውን ወንጀል ሁሉ ለመስራት ተጠቅመውባቸዋል። እቃ እቃ ነው፤ ያረጃል ያፈጃል።ስለሆነም ህወሃት ሲሰፋና ሲደረጅ ሌላ እቃ ቀየረ፤ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ደመቀ መኮንን፣ አለምነው መኮንን፣ ሺፈራው ሽጉጤ፣ ሬድዋን ሁሴን….ስንቱን የቤት እቃ ልቁጠርልህ?
ትልቁ እውነት ወያኔ እቃ መምረጥ መቻሉ ነው። አንተን ፈልገው ሲያገኙህ ተገርሜአለሁ። ከርሱን ለመሙላት ብቻ ሲል የትኛውንም ሃጢያት የሚሰራላቸው ሰው ያልሆነ ሰው ፈልጎ ማግኘት ችሎታቸው የሚሰነቅ ነው። ገና ደጋ ዳሞት አስተማሪ ሳለህ ለቢራና ለምግብ ስትል አያትህን ከሚያክሉ የቡናቤት ባለቤቶች የፈፀምከውን አስነዋሪና አፀያፊ ምግባር አደባባይ ባውለው አንተ ባታፍርበትም ለቤተሰቦችህ ስል እተወዋለሁ።
ይህ ህሊና ቢስነትህ ነው ወያኔ በመብራት ፈልጎ እንዲያገኝህ ያደረገው። የአማራው ክልል ባለስልጣን ሆነህ መሬቱን ለሱዳን እንዲሰጥ በፈረምክ በጥቂት ጊዜ ሚኒስትር አደረጉህ። ምንም ነገር የሚሞሉብህ ባዶ እቃ መሆንህን የበለጠ ባወቁህ ጊዜ ስልጣን አልለውም ለሌላ አገልግሎት ከፍ አደረጉህ። ነገ እንደሌሎች እስኪወረውሩህ። ደመቀ ዝናቡ እንዳይዘንብ አደረጋችሁ ብሎ የሚያወግዛችሁ የለም። ድርቅ የትም ያለ ነው። ርሃብ ግን የጨቋኝ አገዛዝ ውጤት ነው። በቴሌቪዥን ፊት ወጥቶ ርሃቡን ማስተባበል ምን ሊፈይደው ነው። የኃይለስላሴ ሆነ የደርግ አገዛዝ ርሃቡን ሊሸፍኑት አልቻሉም። እንዳለመታደል ሆኖ የእናንተ ጊዜ ደግሞ የበለጠ አስቸጋሪ ነው። ሶሻል ሚድያው፣ የውጭ የዜና አውታሮች፣ ኢሳትና አገር ውስጥ ያሉ ቆራጥ ኢትዮጵያውያን እስካሉ የማይጋለጥ የኢህአዴግ ወንጀል አይኖርም።
በዚህ ቀውጢ ወቅት፣ አንዲት ጠብታ ውሃና ቁራሽ ዳቦ ህይወት ለመታደግ በምትፈለግበት ሰዓት ለህወሃት ባርነት የተገዛችሁበትን ሰላሳ አምስተኛ ዓመት በሶስት መቶ ሚሊዮን ብር ድግስ ለማክበር መነሳታችሁ ብቻ የጭካኔአችሁን መጠን፣ ሆዳምነታችሁንና ህሊናቢስነታችሁን ፍያ አውጥቶባችኋል። ኃይለስላሴ ሰማንያኛ ዓምመታቸውን ለማክበር፣ ደርግ አስረኛውን የአብዮት በዓል ለማስታወስ፤ ያንን ሁሉ ወጪ ማውጣታቸውን በአወገዛችሁበት አንደበት የህወሃትን የ1977 ማሌሊት ምስረታ፣ የህወሃትን አርባኛ ዓመት፣ የብአዴንን ሰላሳ አምስተኛ ዓመት ከረሃብ ጋር እየተያያዘ መምጣትና የእናንተንም አቅል ማጣት በምን ታስተባብሉታላችሁ? በዚች ቅፅበት የወያኔ አገልጋዮችና አለቆቻችሁ ባህርዳር ከተማ ቁንጣን እስኪይዛችሁ ስትበሉ፤ እስከ አጥንቱ የዘረፋችሁት በመላው ዋግ ህምራ፣ በጎንደርና በጎጃም ቆላማ ቀበሌዎች በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናት ደረቁን የእናታቸውን ጡት እየመጠጡ ለዘለዓለሙ በማሸለብ ላይ ናቸው። ወላጆቻቸው አገር ይቀልብ የነበረ ፈርጣማ ክንዳቸው ዝሎና ሟሙቶ፣ ተፈጥሮ ፊቷን አዙራባቸው፣ የልጆቻቸውን ስቃይ ከማየት የማይቀረውን ሞት እየተሳሉ ነውና በምን የሞራል ብቃት ነው እናንተ እየገደላችሁ ላለው አማራ ወኪል የምትሆኑት?
በሶስት መቶ ሚሊዮን ብር ድግስ ህሊናችሁን ልታደነዝዙት ብትታገሉም፣ የአምስት ዓመት ልጇ በርሃብ የሞተባትን ብርቱካን አሊን ከምትኖርበት ሃብሩ ወረዳ ስልሳ ኪሎ ሜትር እርቃ መጥታ ለምለሙ ተሁለደሬ ወረዳ ለጎ ሃይቅ እንድታስተባብል ብታደርጉም፣ መዳ ወላቡ በርሃብ የደከሙ ህፃናትን ብትደባብቁም፣ የአበርግሌውን የእንስሳት እልቂትና የሰውን ህትወት መቀጠፍ መጀመሩን ብትሸፋፍኑም፤ ሥራችሁ የበለጠ እናንተን ከማጋለጥ ሌላ አልጠቀማችሁም። ያለውን እውነት ተቀብሎ ህይወትን ለማዳን ከማንም ጋር መተባበር ግድ የሚልበት ወቅት ላይ ነበራችሁ። ነገር ግን ምርጫችሁ መውደቂያችሁን ማፋጠን ሁኗል። የሁሉም አምባገነን ባህሪይ ነውና፤ መልካም እድል ለቁልቁለቱ ጉዟችሁ እላለሁ።
ደርግን በመሰለ አምባገነን ስርዓትም ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስና አቶ ሽመልስ አዱኛ በየምዕራቡ አገር እንባ አውጥተው ለምነው የሚሊዮኖችን ህይወት አትርፈዋል። ዛሬ እነሱም ሆኑ ቤተሰቦቻቸው አንገታቸውን ቀና አድርገው በህዝቡ መካከል በክብር ይንቀሳቀሳሉ። የፀሃይ ሙቀት ሲዋጀው እንደሚጠፋ ጤዛ ስርዓት በተቀየረ ቁጥር እንደምትጠፉት እንደናንተ እንደካድሬዎች አልነበሩም። አይደሉምም።
ደመቀ! ህወሃት ተጠቅሞብህ የመወርወሩ ጉዳይ ቀኑን አታውቀው እንደሆነ እንጂ የማይቀር ለመሆኑ ከጓደኞችህ እጣ ተረዳ። ሌላ ሌላውን ወንጀል ብትሠራላቸውም፤ በድርቅ በተጎዱ ወገኖች አንተ ስትቀልድና ስታስተባብል ግን ሁላችንን ያመናል። አንተም ደመቀ! ብዬ የፃፍሁልህ ለዚህ ነው። ያንን ሁሉ ስቃይ አልፈው በመጨረሻው የህይወት ዘመናቸው ላይ ያሉትን ዘመዶችህን በክፉ ሥራህ አታሳዝናቸው። ምንም ብታገለግላቸው የአንዱን መሃይም ወያኔ አባል ያክል ክብር ከህወሃት አታገኝም። እቃ እቃ ነው።እቃን ባለቤቱ ይገለገልበታል እንጂ አያከብረውም። ወያኔዎች አንተንና ጓደኞችህን እንደ እቃ እንጂ እንደሌላ እንደማያዩአችሁ ልቦናህ ያውቀዋል።
ለቀሪው ኢትዮጵያውያንም መልዕክት አለኝ። ከክርስቶስ ልደት አራት መቶ ዓመት ቀደም ብሎ የኖረው ታላቁ ግሪካዊ ፈላስፋ ፕሌቶ “one of the penalties for refusing to participate in politics, is that you end up being governed by your inferiors” “በፖለቲካ አልሳተፍም የማለትህ አንዱ ቅጣት፤ በሁለመናቸው የበታቾችህ በሆኑ ስትገዛ መኖርህ ነው” ብሏል። ሁሉንም ነገር ፖለቲካ ነው የምንልና የምንሸሽ ጅሎች እነዚህን በመሰሉ ትንንሾች የመገዛታችን ንግርት በፕላቶ ተነግሮን በተግባር እያየነው ነው።ጥፋቱ የትንንሾቹ ሳይሆን እንዲገዙን የፈቀድንላቸው የእኛ ነው። ደመቀ፣ ኃይለማርያም፣ በረከት፣ ሬድዋን፣ አባይ ወልዱ ሆነ ቴዎድሮስ አድሃኖም ወገኖቻችንን በርሃብ ሲገርፉ፣ ሲዘርፉ የመኖራቸው ምክንያት የእኛው ድክመት ነው።
ድርቁ የምግብ ብቻ አይደለም። ለራስ ነፃነት ለመታገል አለመቁረጣችንም ነው። ይህንን ለመለወጥ እስካልተነሳን ለትንንሾች ስንገዛ፣ አገሪቱም ስትዋረድ ትኖራለች።

No comments:

Post a Comment