Monday, November 9, 2015

ኢህአዴግ በራሱ አባሎች ላይ እርምጃ ሊወስድ ነው

ጥቅምት ፳፰ (ሃያ ስምንት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-በነሃሴ ወር በመቀሌ ከተማ በተካሄደው የግንባሩ 10ኛ ጉባዔ፣ የአባላት ጥራት ጉዳይ አሳሳቢ ሆናል ካለ በሁዋላ በቅርቡ እርምጃ ለመውሰድ መዘጋጀቱን ምንጮች ገልጸዋል፡፡ በግንባሩ ከፍተኛ አመራር ክትትል የሚደረግበት ይህ አፈጻጸም ከላይ አስከታች ድረስ ባሉ መዋቅሮቹ የሚገኙትን ወደ 7 ሚሊየን ይጠጋሉ የተባሉ የግንባሩን አባላት በመገምገም እርምጃ ይወስዳል ተብሎአል፡፡

እንደምንጫችን ገለጻ ከሆነ በዚህ ሒደት እጅግ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አባላት የሚባረሩ ሲሆን ይህንንም ተከትሎ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት አዳዲስ ሹማምንት እንደሚመደቡ ታውቆአል፡፡
ኢህአዴግ በ10ኛ ድርጅታዊ ጉባዔው ላይ የማይናቅ ቁጥር ያላቸው አባሎቹ የአድርባይነት፣ የጠባብነት፣ የትምክህትና የቡድንተኝነት ችግሮች እንዲሁም የተሰጣቸውን ሃላፊነት ከመወጣት ይልቅ በእነዚህ ችግሮች ምክንያት አዝጋሚ አፈጻጸም እያስመዘገቡ መሆናቸውን ይፋ አድርጎ ነበር።
ኢህአዴግ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በከፍተኛ አመራር ውስጥ ጭምር እየታየ መሆኑን በተደጋጋሚ ቢያምንም፣ በተግባር ግን ዋንኛዎቹን ተዋንኖች ደፍሮ በማውጣት በሕግ ተጠያቂ ከማድረግ ይልቅ የታችኖቹን ትንንሽ ዓሳዎች በማጥመድ ለሕዝቡ ለውጥ እያመጣሁ ነው በሚል ተራ አባላትን ጭዳ የማድረግ አቅጣጫ ለመከተል ማሰቡን ምንጫችን አስተያየቱን ገልጿል። በተያያዘ ዜና በአዲስአበባ ከተማ አስተዳደር ከ1 ሺ 600 በላይ የቀድሞ አመራሮች ተባርረው በአዲስ እየተተኩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ የማዘጋጃ ቤቶች አገልግሎት ጨምሮ ማንኛውም ኣይነት ስራዎች እየተከናወኑ አለመሆኑ ታውቆአል፡፡ በብዙ መስሪያ ቤቶች በአንዳንድ ሃላፊዎችና ባለሙያዎች ዘንድ የእንባረራለን ስጋት ከመኖሩ ጋር በተያያዘ ምንም ዓይነት አገልግሎት እየተሰጠ አለመሆኑን ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች አስተያየታቸውን የሰጡ ሲሆን የትሄደው አቤት እንደሚሉም ግራ እንደገባቸው አስታውቀዋል፡፡

No comments:

Post a Comment