Thursday, November 26, 2015

የህንዱ ካራቱሪ ኩባንያ ንብረት ጨረታ ወጣበት

 ኢሳት ዜና :-የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጋምቤላ ብሔራዊ ክልል በኑኤር ዞን ጂካዎ እና ኢታንግ ወረዳ የሚገኘውን የህንዱ ካራቱሪ አግሮ ፕሮዳክትስ ኃ/ተ/የግ/ማ ንብረት የሆነውን 100ሺህ ሄክታር የእርሻ መሬት ጨምሮ ሌሎች ንብረቶች ላይ የሐራጅ ጨረታ አውጥቷል።

ባንኩ ህዳር 7ቀን 2008 በመንግስታዊው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ባወጣው የሐራጅ ማስታወቂያ መሠረት ተጨራቾች እስከ ታህሳስ 12 ቀን 2008 ዓ.ም ድረስ መጫረት እንደሚችሉ የገለጸ ሰሆን፣ በዚህ ጨረታ ለሽያጭ የቀረበው የካራቱሪ በሊዝ የተረከበው መሬት 100 ሺ ሔክታር ሲሆን ከዚህ ውስጥ 7ሺ 645 ሄክታር መሬት የለማ መሆኑን ገልጾአል፡፡ ኩባንያው ከመንግስት ለእርሻ ኢንቨስትመንት ከተረከበው መሬት በተጨማሪም መጋዘን፣ የሠራተኞች መኝታ ቤቶችንና ተገጣጣሚ ቤቶችን ባንኩ እንደሚሸጥ አስታውቆአል፡፡ ባንኩ ያስቀመጠው የጨረታ መነሻ ዋጋ 55 ሚሊየን 886 ሺህ

424 ብር ከ52 ሳንቲም ነው፡፡ ካራቱሪ ኩባንያ ከኢትዮጽያ ንግድ ባንክ ከ 4 አመት በፊት 62 ሚሊየን ብር የተበደረ ሲሆን ገንዘቡን ለተወሰነ ጊዜያት መክፈል ከጀመረ በሃላ ማቁዋረጡን ከባንኩ የተገኘ መረጃ ይጠቁማል፡፡
ኩባንያው ከስምንት ዓመት በፊት ወደኢትዮጵያ ገብቶ እጅግ ሰፊ መሬት በርካሽ ሊዝ ዋጋ ሲወስድ «ይህ ክስተት በርካታ ገበሬዎችን ያፈናቅላል፣ ለተፈጥሮ ሐብት ውድመትም ያጋልጣል» በማለት ሲቃወሙ የነበሩ ኢትዮጵያዊያንን«የጸረ ልማት ሃይሎች አጀንዳ ነው» በማለት መንግስት ሲያጣጥል ቆይቷል።
ኩባንያው በሜካናይዜድ የግብርና ስራ ብዙ ውጤት ያመጣል በሚል እምነት በነጻ በሚል የሊዝ ዋጋ 300ሺህ ሄክታር መሬት በጋምቤላ ክልል ከዛሬ ሰባት ዓመት በፊት እንዲረከብ የተደረገ ሲሆን፣ ኩባንያው በፍጥነት ወደስራ
እገባለሁ በሚል የተረከበው ቦታ ላይ ያሉትን ዛፎችና ሌሎች የተፈጥሮ ሐብቶች በማውደሙ ከአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቶች በወቅቱ ከፍተኛ ተቃውሞ ደርሶበታል፡፡ ይህም ሆኖ ኩባንያው ስራውን በይፋ እስካቆመበት ጊዜ ድረስ
ከተሰጠው ቦታ ማልማት የቻለው 800 ሄክታር መሬት ብቻ ነው፡፡በዚህ ምክንያት ከአንድ ኣመት ተኩል በፊት የግብርና ሚኒስቴር 200 ሺ ሄክታር መሬት ከኩባንያው መልሶ ለመቀማት ተገዶኦል፡፡
ኩባንያው ከ150 በላይ ቋሚና ጊዜያዊ ሰራተኞች የነበሩት ሲሆን የሀገሪቱን ሕግ አክብሮ የሠራተኛ መብት በማክበር መክፈል የነበረበትን የደመወዝ ገቢ ግብር ባለመክፈሉ ተጨማሪ ክሶች አሉበት፡፡በተጨማሪም በግብርና ኢንቨስትመንት
ለመሰማራት ፈቃድ ወስዶ፣ ከባንክ በተበደረው ገንዘብ ከቀረጥ ነጻ ያስገባቸውን የእርሻ ማሽነሪዎችን ለሶስተኛ ወገን በማከራየትና በመሸጥ ያልተፈቀደለት ንግድ ስራ ውስጥ ገብቶም መገኘቱ ስለኩባንያው ብዙ ያወራውን መንግስት ጭምር ያሳፈረ ሕገወጥ ተግባር ሆኗል፡፡
ካራቱሪ ቦታውን የተረከበው ከፌዴራል መንግስት በመሆኑ የጋምቤላ ክልላዊ መንግስት ብዙ ችግሮች መኖራቸውን ቢረዳም ምንም ማድረግ ሳይችል ቀርቷል።የኩባንያው ከፍተኛ ሃላፊዎች ከመንግስት በሊዝ ኪራይ ያገኙትን መሬት
በማስያዝ ከንግድ ባንክ ከተበደሩና ሕገወጥ ስራ ሲያከናውኑ ከቆዩ በሁዋላ ጉዳዩ ሲታወቅባቸው ሀገር ለቀው መውጣታቸው ታውቆአል፡፡

No comments:

Post a Comment