Saturday, November 14, 2015

የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች ተማሪዎችን በብሄር ብሄረሰቦች መብት ዙሪያ እንዲያወያዩ ታዘዙ

ኀዳር ፫ (ሦስት) ቀን ፳፻፰ ዓ/ም ኢሳት ዜና :- ኢሳት በትምህርት ሚኒስቴር የአስተዳደር ጉዳዮች ሃላፊ በሆኑት በዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ ኪዳኔ ተጽፎ ለእያንዳንዱ ዩኒቨርስቲ የተሰራጨው የኢሜል መልእክት ከኢሳት የትምህርት ሚኒስቴር ምንጮች የደረሰው ሲሆን፣ የዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንቶች በሞላ ተማሪዎችን ህዳር 29 ለሚከበረው 10ኛው የብሄር ብሄረሰቦች በአል እንዲያወያዩ ታዘዋል።

በቀረበው የውይይት ሰነድ በተራ ቁጥር 7 ላይ ከዩኒቨርስቲ ተማሪዎች የሚጠበቀው ግዴታ ምን እንደሆነ በዝርዝር ቀርቧል።
ሰነዱ ” ቀደምት የተማሪ ትውልዶች የብሄሮችና ብሄረሰቦች መብት በመታፈኑና የዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች በመረገጣቸው ደምተው አጥንታቸውን ከስክሰውና የሕይወት መስዋዕትነት ከፍለው የዴሞክራሲ ሥርዓትን እውን አድርገዋል፤ልማታዊ መንግሥት አቋቁመዋል፤ ተስፋ ሰጪና ሕዝብ በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆንበትን የልማት ጅምሮች መሠረት ጥለዋል፡፡ተጨባጭ ሁኔታው ይህ በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ ሀገራዊ ሚና ተለውጧል” ይላል።

የውይይቱ ሰነድ በመቀጠልም ” የአሁኑ ትውልድ ኃላፊነት እንደ ቀደምቱ ትውልድ የጦር መሣሪያ አንስቶ በረሀ መግባት ሣይሆን፣ በሁሉም ዘንድ መግባባት የተደረሰበትን ሀገሪቱን ከከፋው የድህነት አረንቋ ለማውጣት የራሱን ድርሻ መወጣት ነው፡፡ ትምህርት ቤቶች የትምህርት ማዕከላት መሆናቸውን በመገንዘብ ፀጥታቸው እንዳይደፈርስና ምንም ዓይነት ኢ- ሕገ መንግሥታዊ ተግባራት እንዳይፈጸሙባቸው መታገል ይኖርበታል፡፡” በማለት ተማሪው ባለው ስርዓት ላይ ምንም አይነት ተቃውሞ እንዳያነሳ ያስጠነቅቃል።
ተማሪው ” ከሁሉም በላይ ሕገ መንግሥቱን የማክበርና የማስከበር ሚናውን በእውቀትና በፍላጎት ላይ በተመሠረት ማከናወንና በብዙ መስዋዕትነት የተገነባውን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መጠበቅና ሥርዓቱ እንዲጎለብትም ተሣትፎውን ማጠናከር ይኖርበታል፡፡” በማለት ተማሪዎችና መምህራን መፈጸም ያሉባቸውን ግዴታዎች ይዘረዝራል።
ሰነዱ ኢህአዴግ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ታልቃ መግባቱን ብቻ ሳይሆን፣ ትምህርት ቤቶችንና አስተዳደሩን የካድሬ መፈልፈያ ለማድረግ ታጥቆ መነሳቱን ያሳያል በማለት ሰነዱን የላኩት ምንጮች አስተያየታቸውን አስፍረዋል።
በሌላ ዜና ደግሞ በሰሜን ጎንደር ካለፉት ሶስት ሳምንታት ጀምሮ የተዘጉ ትምህርት ቤቶች አሁንም ስራ አልጀመሩም። በአካባቢው የተነሳውን ተቃውሞ ተከትሎ የጸጥታ ሃይሎች በህዝቡ ላይ እየወሰዱ ያለው አስከፊ እርምጃ፣ ተማሪዎች ወደ ተለያዩ አካባቢውዎች በመሸሻቸው እንዲሁም የጸጥታው ሁኔታ ትምህርት ለማስጀመር ባለማስቻሉ ትምህርት ቤቶች እንደተዘጉ ነው።

No comments:

Post a Comment