Wednesday, January 28, 2015

አንድነት ፓርቲ በድጋሜ የተቃውሞ ሰልፍ ጠራ

ጥር ፲፱(አስራ ዘጠኝ) ቀን ፳፻፯ ዓ/ም ኢሳት ዜና :-ፓርቲው ባወጣው መግለጫ ህወሃት /ኢህአዴግ ጥር 17/2007 ዓም በአንድነት አመራሮችና አባላት ላይ ያደረሰውን አሰቃቂ ድብደባ ለማውገዝ እንዲሁም ፓርቲውን ለመቀማት የሚደረገውን ጥረት ለማውገዝ ለጥር 24 በአዲስ አበባና በሌሎች የተለያዩ የክልል ከተሞች ላይ ሰልፍ ለማድረግ ማቀዱን ገልጸሏል።
አምባገነኑ የህወሀት/ኢህአዴግ መንግስት የዘንድሮውን ሀገራዊ ምርጫ ሂደቱንም ጭምር በማበላሸት ጠንክራ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከምርጫው ውጪ እንዲሆኑ ለማድረግ ላይ ታች እያለ ነው የሚለው አንደነት ፓርቲ፣ በምርጫ ቦርድ፣ በኢቲቪ እና በሬዲዮ ፋና የሶስትዮሽ ግንባር በመክፈት በህዝቡ ዘንድ ብዥታ እንዲፈጠር፣ ምርጫው ያለጠንካራ ተዋዳደሪ እንዲካሄድ በማድረግ የምርጫውን ዋጋ ቢስነት አረጋግጧል ብሎአል።
አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ ለሚካሄደው ሰልፍ ደብዳቤ ማስገባቱን የፓርቲው የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ አስራት አብርሃ ገልጿል። መስተዳድሩ በእለቱ የአፍሪካ ህብረት ስብሰባ መኖሩን ገልጾ ሰልፉን አለመፍቀዱን ቢያስታውቅም፣ አንድነት ፓርቲ የመስተዳድሩን ሃሳብ አለመቀበሉን አቶ አስራት አክለው ገልጸዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ምርጫ ቦርድ የምዝገባ ጣቢያዎች በሰዎች ድርቅ በተመቱበት በዚህ ወቅት ይመዘገባል ብሎ ከሚጠብቀው 35 ሚሊየን መራጭ ውስጥ ባለፉት 14 ቀናት ብቻ ከ28 ሚሊየን በላይ ተመዘገበ ማለቱ አነጋጋሪ ሆኗል።
አንድነትና መኢአድ በምርጫ ቦርድ በተሰራባቸው ሴራ ምክንያት በመጪው ምርጫ የመሳተፋቸው ነገር አጠራጣሪ ሆኖአል፡፡ በመጪው ረቡዕ ወይም ሐሙስ ምርጫ ቦርድ ፓርቲዎቹን ባስቀመጥኩት ቀነ ገደብ መሰረት ማሟላት የሚገባቸውን ነገሮች አላሟሉም በሚል ከምርጫ ተሳትፎ የሚያግድበትን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል መረጃዎች ያመለክታሉ።


No comments:

Post a Comment