Wednesday, January 21, 2015

ሥርዓቱ የምርጫ ካርድ ያልወሰዱትን ስኳር በመከልከል ማስፈራራት ጀምሯል

(ነገረ ኢትዮጵያ) በምስራቅ ጎጃም ዞን አነደድ ወረዳ የቦቀል ቀበሌ ነዋሪዎች የምርጫ ካርድ ስልልወሰዳችሁ ስኳር አይሰጣችሁም መባላቸውን ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ በአካባቢው ስኳርን ጨምሮ ሌሎች አቅርቦቶች በስፋት እንደሚጠፉ የተናገሩት ነዋሪዎቹ ዛሬ ጠዋት የቀበሌ ካድሬዎች በድምጽ ማጉያ ‹‹ዛሬ ስኳር ስለመጣ ቀበሌ ድረስ መጥታችሁ እንድትወስዱ፡፡ የመጣው ስኳር ውስን በመሆኑ ሊያልቅ ስለሚችል ዛሬውኑ መጥታችሁ እንድትወስዱ እናሳስባለን፡፡ ከዛሬ ውጭ ላታገኙ ትችላላችሁ፡፡›› እያሉ ሲለፉ እንዳረፈዱ ተናግረዋል፡፡

ሆኖም መጥቷል የተባለው ስኳር ለማግኘት ወደ ቀበሌው ያመሩት ነዋሪዎቹ ስኳሩን ለመውሰድ ሲጠይቁ ‹‹የምርጫ ካርድ ወስዳችኋል?›› የሚል ጥያቄ እንደሚቀርብላቸው ግልጸዋል፡፡ የምርጫ ካርድ የሚያሳዩ ነዋሪዎች ስኳሩ ሲሰጣቸው፤ ያላወጡት በአስቸኳይ ምርጫ ካርድ አውጥተው እንዲመለሱና ስኳር እንዲወስዱ ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡ በአንጻሩ ስኳር ለመውሰድ የምርጫ ካርድ ማውጣት የለብንም ያሉት ነዋሪዎች ስኳር እንደማያገኙ የተነገራቸው ሲሆን ‹‹እንደዜና የምርጫ ካርድ ወሰድንም አልወሰድንም ስኳር የማግኘት መብት አለን›› ያሉ ዜጎች በፖሊስ ተደብድበው እንደተባረሩ ከቦታው የደረሰን መረጃ ያመለክታል፡፡

በጠዋቱ የቀበሌ ነዋሪዎች ያሰሙት የነበረውን ለፈፋ ሰምቶ ወደ ቀበሌ ያመራ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ መምህር የምርጫ ካርድ ካላመጣ ስኳር እንደማይሰጠው ተነግሮት መመለሱን ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጾአል፡፡ መምህሩ ‹‹የምርጫ ካድር የመውሰድና ያለመውሰድ መብት አለኝ፡፡ የማምንበት ፓርቲ ሲኖር የምርጫ ካርድ እወስዳለሁ፡፡ ካልሆነ ግን አልወስድም፡፡ ብወስድም ስኳር ለማግኘት ብዬ አይደለም፡፡ እንደማንኛውም ዜጋ ስኳር የማግኘት መብት አለኝ፡፡›› በሚል የቀበሌ ሰራተኞቹን ለማስረዳት ቢሞክርም ‹‹እኛ ስኳር ስጡ የተባልነው ካርድ ለወሰደ ብቻ ነው፡፡ ካርድ ካልወሰድክ አይሰጥህም›› ተብሎ እንደተመለሰ ገልጾልናል፡፡


No comments:

Post a Comment