Thursday, January 8, 2015

በሰማያዊ አባል ላይ የአቃቤ ህግ ምስክር ተሰማ

•‹‹መንግስትን የሚቃወም ወረቀት ሲበትን ይዘነዋል›› የአቃቤ ህግ ምስክሮች
በነገረ ኢትዮጵያ ሪፖርተር
ህዳር 27 እና 28/2007 ዓ.ም በ9ኙ ፓርቲዎች ትብብር ተዘጋጅቶ ለነበረው የአዳር ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ የቅስቀሳ በራሪ ወረቅት ሲበትን ለእስር የተዳረገው የሰማያዊ ፓርቲ አባል በፌደራል አቃቤ ህግ ክስ እንደቀረበበት የሚታወስ ሲሆን፣ አቃቤ ህግ ምስክር ያላቸውን አቅርቦ አስመስክሯል፡፡
ታህሳስ 30/2007 ዓ.ም በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መናገሻ ምድብ 2ኛ ወንጀል ችሎት የቀረበው የሰማያዊ ፓርቲ አባል አቶ ሲሳይ ዘርፉ ‹‹…‹ነጻነት ለፍትሓዊ ምርጫ› ለመላው ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያዊ ሁሉ….ተብሎ የተጻፈበት በራሪ ወረቀቶች ለህብረተሰቡ ሲያከፋፍል እጅ ከፈንጅ በመያዙ በፈጸመው የሐሰት ወሬን በማውራት ህዝቡን ማነሳሳት ወንጀል…›› በፌደራል አቃቤ ህግ ተከስሶ ጉዳዩን እየተከታተለ እንዳለ ይታወሳል፡፡
በመሆኑም ታህሳስ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የአቃቤ ህግ ሁለት ምስክሮች ቀርበው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አን
ደኛ ምስክር ሆኖ የቀረበው ኮንስታብል ያለው መንግስቴ፣ ‹‹ተከሳሹን ህዳር 24 ቀን 2007 ዓ.ም ከምሽቱ 12፡00 ላይ መንግስትን የሚቃወም በራሪ ወረቀት ሲበትን አይተነዋል፤ በዚህም ወረቀት ሲበትን ያገኛችሁትን ሰው ያዙ ተብልን ስለነበር ተከሳሹን በቁጥጥር ስር አውለነዋል›› ብሏል፡፡ መስካሪው በወቅቱ ተከሳሹን ሲይዙት የፖሊስ ደንብ ልብስ እንዳልለበሱና በሲቪል እንደነበሩ ገልጾ፣ ‹‹የሚበተነው ወረቀት በዘጠኙ ፓርቲዎች መዘጋጀቱን እንጂ ይዘቱን አላስታውሰውም፤ የህግ አስከባሪ እንደመሆኔ ግን ተከሳሹን በቁጥጥር ስር እንዲውል አድርጌያለሁ›› ሲል ምስክርነቱን ለችሎቱ አስረድቷል፡፡
ሁለተኛ የአቃቤ ህግ ምስክር ሆኖ የቀረበው ኮንስታብል ማርክሽ ሹመሌ በበኩሉ፣ ‹‹ሲቪል ነበር የለበስኩት፤ ተከሳሹ ወረቀት ሰጠኝ፡፡ ሳየው መንግስትን የሚቃወም ወረቀት ነው፡፡ ወረቀቱን ለጓደኛዬ አሳየሁት፡፡ ከዚያም በቁጥጥር ስር አዋልነው›› ሲል ለችሎቱ ተናግሯል፡፡
አቃቤ ህግ ሁለቱ ምስክሮች የሰጡትን ምስክርነት ከተያዘው በራሪ ወረቀት ጋር አገናዝቦ በተከሳሽ ላይ የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥለት ፍርድ ቤቱን ጠይቋል፡፡ ተከሳሽ በበኩሉ ‹‹መንግስትን መቃወም ህገ-መንግስታዊ መብቴ ነው፡፡ ስለሆነም ወንጀል አልሰራሁም›› ሲል ተከራክሯል፡፡
ሆኖም ግን ዳኛው በበራሪ ወረቀቱ ላይ የተጠቀሰውን ‹‹የኢህአዴግ መንግስት ያፍናል፣ ያጭበረብራል፣ ይገድላል…›› በማውሳት ድርጊቱ ወንጀል ስለሆነ ተከሳሹ መከላከል አለበት ሲል ወስኗል፡፡ ስለሆነም ተከሳሽ አቶ ሲሳይ ዘርፉ መከላከያ ምስክሮቹን (የሰነድም) ይዞ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቱ ለጥር 7/2007 ዓ.ም ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡


No comments:

Post a Comment