Wednesday, January 21, 2015

በባህር ዳር ሲካሄድ የነበረው የመምህራን ስልጠና ያለስምምነት ተጠናቀቀ፤ መንግስት ስልጣኑን እንዲያስረክብ ተጠየቀ።

ኢሳት ዜና ፦ በባህር ዳር ከተማ ለከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ እና መሰናዶ ትምህርት ቤቶች መምህራን ሲካሄድ የቆየው ስብሰባ የታሰበለትን ዓላማ ሳያሳካ መጠናቀቁን በስፍራው የሚገኘው የኢሳት ወኪል ያጠናቀረው መረጃ ያመለክታል። መንግስት ሰሞኑን ትምህርት ቤቶችን ለአንድ ሳምንት በመዝጋት ለግልና ለመንግስት መምህራን ሲሰጠው የቆየው ስልጠና በሚጠናቀቅበት ጊዜ መምህራን በተሰጡት በሁሉም ርዕሶች ላይ ስምምነት ላይ ሳይደርሱ ስልጠናው መጠናቀቁን በስብሰባው የተሳተፉ መምህራን ለዘጋቢያችን ገልጸዋል። በክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣናት በተዘጋጁት ሰነዶች ላይ የተወያዩት የኢኮኖሚክስ ምሁራን ፦ «ኢትዮጵያ ባለፉት 12 ዓመታት ባለ ሁለት አሃዝ የኢኮኖሚ እድገት በማሳየት ካደጉ ሃገሮች ተርታ ተሰለፋለች።» በሚል ርእስ ያቀረቡትን ሰነድ አልተቀበሉትም። ኢትዮጵያ አሳየች የሚባለው እድገት ትክክለኛው እድገት ሳይሆን የመንግስት የቁጥር ጨዋታ መሆኑን ኢኮኖሚስቶቹ በምሁራዊ ትንተና አስደግፈው ለተሰብሳቢ መምህራን ሙያዊ ማብራሪያ መስጠታቸውን እና በድፍረት መናገራቸውን ፤ በስብሰባው የተሳተፉ መምህራን ለዘጋቢያችን ገልጸዋል።



ሰልጣኝ መምህራኑ አክለውም፦ «በኢህአዴግ ታቅፋችሁ የምትሰሩ አመራሮች በሶስት ምክንያት ነበር። እነሱም የድርጅት ፍቅር፣የስልጣን ፍቅርና የገንዘብ ፍቅር ነበሩ። ሆኖም በአሁኑ ሰዓት የድርጅት ፍቅሩ እየከሰመ መጥቶ ድርጅቱ ለስልጣንና ለገንዘብ የሚሰባሰቡበት፣ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ ሳይሆን ሹመኞች የራሳቸውን ሃብት የሚያካብቱበት የጥቂቶች ፓርቲ ሆኗል።» በማለት መናገራቸውን እስከመንገር ደርሰዋል። ስብሰባውን ሲመሩ የነበሩት ካድሬዎች በመምህራኑ በኩል የሚመጡትን ጥያቄዎች፣ ተቃውሞዎችና ሙያዊ ማብራሪያዎች መቋቋም ተስኗቸው እንደነበር መምህራኑ ተናግረዋል። በቀረበው ሰነድ በተለይ ሀሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትና የመቃወም መብት ስለመረጋገጡ፣ የዜጐች የነፍስ ወከፍ ገቢ እና አማካይ የህይወት ዘመን ስለመጨመሩ የተቀመጠውን ምሁራኑ አጥብቀው ተቃውመውታል።

እንዲሁም በሰነዱ ላይ፦«የኢትዮጵያ ትንሳዔ እውን መሆን ጀምሯል» መባሉን ያልተቀበሉት ሰልጣኞቹ፦«የኢትዮጵያውያን ሃብት በጥቂት የስርአቱ ደጋፊዎችና በከፍተኛ አመራሩ እጅ ተይዞ እያለ፤ እንዴት የኢትዮጵያ ትንሳኤ እውን መሆን ጀምሯል ትላላችሁ?» በማለት በድፍረት ተናግረዋል። በተለይ በመጨረሻ የስብሰባው ቀን ማለትም በዕለተ አርብ በተደረገው ውይይት በሁሉም መድረኮች ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰምቷል። የገዢው መንግስት የኢትዮጵያን ህዝብ ለመምራት የሚያስችለው አቅምና እውቀቱ ተሟጦ ያለቀበት መሆኑ በሚያሳያቸው የአመራር ጉድለቶችና ሰብአዊ መብት አያያዝ ሂደቱ እየታዩ በመሆናቸው፤ ያለምንም ግርግር ለተተኪው ትውልድ ስልጣኑን በሰላማዊ መንገድ እንዲያስረክብ የሚጠይቅ ግልጽ ጥያቄ በመምህራኑ ቀርቧል።


No comments:

Post a Comment