Wednesday, May 11, 2016

በኢትዮጵያ የተሰከሰተው ድርቅ በህጻናት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰ ነው ተባለ

ኢሳት (ግንቦት 3 ፥ 2008)

በኢትዮጵያ በተከሰተው ከፍተኛ የዝናብ እጥረት የህጻናትን ህይወት ለአደጋ እያጋለጠ መገኘቱን   ዩኒሴፍ አስታወቀ።የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጀት UNICEF ይህንን ያስታወቀው በሳምንቱ መጀመሪያ በድረ ገጹ ላይ ባቀረበው ዘገባ ሲሆን፣ህጻናቱም ሆነ ቤተሰቦቻቸው ችግሩን ለመቋቋም ቀዬያቸውን ጥለው ለመሰደድ መገደዳቸውንም አስፍሯል።

ባለፈው ዓመት ዝናብ በወቅቱ ባለመዝነቡ ምክንያት የውሃ እጥረት እና የአዝመራ መውደም እንዳስከተለ፣ ይህም የህጻናት ምግብ አቅርቦት በእርዳታ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ማድረጉንም ዩኒሴፍ አስታውቋል። ህጻናትና ቤተሰቦቻቸውም ችግሩን ለማቋቋም የተለየ መፍትሄ መፈለግ መገደዳቸውን ሪፖርቱ በምስል አስደግፎ አስፍሯል። በድርቁ የተጎዱ ቤተሰቦችም ቀያቸውን እየለቀቁ ወደሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ እንደሆነ የገለጸው ይህ ዘገባ፣ በተለየ መልኩ የተጎዱት አርብቶ አደሮችም ከብቶቻቸው እየሞቱባቸው መሆኑንና፣ ለቀሪዎቹ እንስሳት መኖና ውሃ ለማግኘት ሲሉ ቀያቸውን ጥለው እጅግ ራቅ ወደአሉ ወዳሉ አካባቢዎች እየሄዱ እንደሆነ በምስል ተደግፎ የቀረበው ዘገባ ያስረዳል።
አቶ ቦራ ሮቡ ኢቱ የተባሉ በኦሮሚያ ክልል የሚኖሩ አርብቶ አደር ሲናገሩ በየቀኑ ለሶስት ሰዓት ውሃ ፍለጋ እንደሚንከራተቱና በሁለተኛው ቀን ወደቤተሰቦቻቸው እንደሚመለሱ ዩኒሴፍ በዘገባው አመልክቷል።ዘገባው በመቀጠልም ድርቅ ባጠቃቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ተማሪዎችም ትምህርታቸው ትተው ወላጆቻቸውን ለመርዳት ከትምህርት ገበታቸው እንደሚቀሩ ገልጾ፣ እነዚሁ ልጆች ቆሻሻ ውሃ በመጠጣትም ለተለያዩ የውሃ ወለድ በሽታ ተጠቂ መሆናቸው ተገልጿል።
በእነዚህ አካባቢዎች ድርቅ መከሰት በተማሪዎች የወደፊት ህይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እያደረሰ እንደሆነ ለዩኒሲፍ የተናገሩት በሃሮ ሁባ ኮሚውኒቲ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩ መምህር ሲሆኑ፣ተማሪዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ የማይገኙት ወይ ውሃ ፍለጋ በመሄዳቸው፣አሊያም ከቀያቸው ራቅ ወዳለ ስፍራ ከነቤተሰቦቻቸው በመሰደዳቸው እንደሆነ አመልክተዋል።
ሃርኮ የምትባል የ12 አመት ተማሪም ከወንድሟ ጋር በመሆን በየቀኑ ውሃ ፍለጋ ስለምትሄድ ትምህርቷን እንዳቋረጠች በዘገባው ተጠቅሷል። ሃርኮ ከታላቅ ወንድሟ ጋር በመሆን፣ ሙቀቱን ለመቋቋም በምሽት እንደምትጓዝና ወደቤተሰቦቿ በሚቀጥለው ቀን እንደምትመለስም በዩኒሴፍ ዘገባ ተመልክቷል።
በኦሮሚያ ክልል አርብቶ አደር አካባቢዎች ሰዎች ውሃ ለማግኘት እስከ 10 ሰዓት ድረስ እንደሚጓዙና ውሃ በሚገኝበት አካባቢም ህጻናት ከእንስሳት ጋር ከአንድ ጉድጓድ እንደሚጠጡም ተገልጿል። እነዚህ ህጻናትም ለተቅማጥና የጀርባ ህመም እንደሚጋለጡም ዩኒሴፍ በፎቶ ባስደገፈው ዘገባ አስረድቷል።

No comments:

Post a Comment